ባለፈው ዓመት፣ የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተናን የማለፊያ ነጥብ ያላመጡ ከ600ሺሕ በላይ ተማሪዎች፣ ዘንድሮ ወደ ቴክኒክ እና ሞያ ማሠልጠኛ ተቋማት እንደሚገቡ፣ መንግሥት አስታወቀ፡፡
ይህን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት፣ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል፣ ተማሪዎቹ የሚሠለጥኑት፣ በዐዲሱ የትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ መሠረት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
ዐዲሱ የሥልጠና ፖሊሲ፣ ከዚኽ ቀደም፣ እስከ ደረጃ-5 ድረስ የነበረውን የቴክኒክ እና ሞያ ሥልጠና ዕርከን፣ እስከ ደረጃ-8 ድረስ እንዳሳደገው ጠቅሰው፣ የመጨረሻው ደረጃ-8፥ ከሦስተኛ ዲግሪ አቻ ግምት እንደሚተካከልም፣ ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡት የዘርፉ ባለሞያ ዶር. አዳነ አበጀ ደግሞ፣ ውሳኔው፥ የተማሪዎችን ፍላጎት ከግምት ማስገባት እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
በቴክኒክ እና ሞያ ማሠልጠኛ ተቋማት ላይ የግንዛቤ እና የአመለካከት ችግር አለ፤ የሚሉት ዶር. አዳነ፣ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ከተፈለገ፣ ይህን ችግር መቅረፍና ተቋማቱ ያሉባቸውን የቴክኖሎጂ እና የዐቅም ክፍተት መሙላት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።