በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ በጋራ በመስተናገድ ላይ ባለው የዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ የመክፈቻዎቹ ውድድሮች፣ ከአፍሪካውያኑ ቡድኖች አንዳቸውም አሸናፊ አልኾኑም።
የሞሮኮው “የአትላስ አንበሶች” የሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ በጀርመን 6 ለ 0 መሸነፉ፣ የደጋፊዎቹን ልብ ሰብሯል። ከ“አትላስ አንበሶቹ” ቀደም ብሎ የመክፈጫ ጨዋታቸውን ያደረጉት፣ ደቡብ አፍሪካ በስዊዲን 2 ለ 1 ስትሸነፍ፣ ዛምቢያ ደግሞ በጃፓን 5 ለ 0 ውጤት ተረትታለች። ናይጄሪያ ከካናዳ ጋራ ባደረገችው የመክፈቻ ጨዋታ ደግሞ ባዶ ለባዶ ተለያይታለች፡፡
የመክፈቻ ጨዋታ ውጤቶቹ እንደታዩት ቢኾኑም፣ የቡድኖቹ አሠልጣኞች ግን፣ ወደሚቀጥለው ዙር እንደሚያልፉ ይተማመናሉ። የዛምቢያው ቡድን አሠልጣኝ ብሩስ ምዋፔ፣ ከጃፓን ጋራ ባደረጉት ግጥሚያ፣ ቡድኑ በሚገባ አለመጫወቱን ተናግረው፣ በቀጣይ ጨዋታዎች ጥሩ ውጤት እንደሚያገኙ ይተማመናሉ። ዛምቢያ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የምትችለው፣ ከስፔን እና ኮስታ ሪካ ጋራ ያላትን ጨዋታዎች በአሸናፊነት ከወጣች ነው።
የደቡብ አፍሪካው አሠልጣኝ ዴሲሬ ኤሊስ፣ የዛምቢያውን አሠልጣኝ ሐሳብ ይጋራሉ። ቡድናቸው፣ በዓለም ምርጥ ተጨዋቾችን በመያዙ፣ ከአርጄንቲና እና ጣልያን ጋራ ወደፊት በሚኖራቸው ጨዋታ፣ ግሩም ውጤት ያገኛሉ፤ ብለው ይጠብቃሉ።
የናይጄሪያው “ሱፐር ፋልኮንስ”፣ ከካናዳ ጋራ ባዶ ለባዶ በመውጣታቸው፣ ነጥብ ለመጋራት ችለዋል። ከአፍሪካ ቡድኖች ውስጥ፣ እስከ አሁን ነጥብ ያለው ብቸኛው ቡድን መኾኑ ነው። ከአውስትራሊያ እና ከአየርላንድ ጋራ በሚያደርጉት ጨዋታ ሳይሸነፉ ከወጡ፣ ወደሚቀጥለው ዙር የማለፍ ዕድል ይኖራቸዋል።
የአሜሪካው የሴቶች ቡድን፣ ያለፈው የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን ሲኾን፣ አሁንም ድሉን እንዲደግም በኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ ትልቅ ድጋፍ ያለው ቡድን ነው። አሜሪካ ይህን ዋንጫ ካሸነፈች፣ በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ፣ ሦስት ጊዜ በተከታታይ ያሸነፈች ብቸኛ ሀገር ያደርጋታል።