የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት ረቡዕ በወሰዱት ርምጃ፣ በመደበኛ ሥያሜያቸው ‘አንሳር አላህ’ በሚል መጠሪያ የሚታወቁትን የየመኑን ሁቲዎች በውጭ አሸባሪ ድርጅትነት እንዲፈረጁ ማዘዛቸውን ዋይት ሀውስ አስታወቀ። ርምጃው በኢራን የሚደገፈው ቡድን በቀይ ባህር በሚተላለፉ የንግድ መርከቦች እና ወሳኝ ለሆኑት የባህር ኬላዎች ከለላ እና ጥበቃ በሚያደርጉ የዩናይትድ ስቴትስ የጦር መርከቦች ላይ ለሚያደርሷቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች የባይደን አስተዳደር ወስዶት ከነበረው ምላሽ የበረቱ የኢኮኖሚ ገደቦችን የሚጥል መሆኑ ተመልክቷል።
ዋይት ሀውስ በመግለጫው አክሎም “የሁቲዎች እንቅስቃሴ በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ በአሜሪካውያን ሲቪሎች እና ሠራተኞች ደኅንነት፣ በክልሉ የሚገኙ የቅርብ አጋሮቻችን እና ብሎም ዓለም አቀፍ የባህር ንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ አደጋ የደቀነ ነው” ብሏል።
‘ርምጃውን የሚደግፉ ወገኖች እስካሁንም መደረግ የነበረበት ነው’ ሲሉ፤ የጉዳዩ አዋቂዎች በበኩላቸው የርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ ሁቲዎችን ከመደገፍ የሚቆጠር ሥራ የሠራ ማንኛውንም ወገን ለቅጣት ሊዳርግ የሚችል ነው ይላሉ። አብዛኛውን የመን ግዛቶች የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከኅዳር 2023 ዓ.ም አንስቶ እስራኤል ጋዛ ውስጥ ከሃማስ ጋራ እያደረገች በነበረው ጦርነት ከፍልስጤማውያን ጋራ በማበር ቀይ ባህር ላይ በሚጓጓዙ መርከቦች ላይ ከ100 በላይ ጥቃቶች አድርሰዋል። በጥቃቶቹም ሁለት መርከቦችን ሲያሰጥሙ፣ አንዲት መርከብ በመያዝ፤ አራት መርከበኞችን ገድለዋል። በተጨማሪም በጥቃቱ ዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞዎችን በማስተጓጎል የንግድ ድርጅቶች ለአንድ ዓመት ያህል ጥቃቶቹን ለመሸሽ በደቡባዊ አፍሪካ ዞረው ረዥም እና ከፍ ያለ ዋጋ የሚያስከፍሉ ጉዞዎችን እንዲያደርጉ አስገድደው እንደ ነበር ይታወቃል።