በዩክሬን ክራማቶርስክ ከተማ በሚገኝ ሆቴል ላይ በደረሰ ጥቃት የሮይተርስ የዜና ወኪል ቡድን አባል ሲገደል ሌሎች ሁለት ሰዎች ቆስለዋል።
ሮይተርስ እንዳስታወቀው፣ ራያን ኢቫንስ የተሰኘው የዘጋቢ ስምሪት ቡድኑ የደህንነት አማካሪ የተገደለው፣ያረፈበት ሆቴል በሚሳይል በመመታቱ ነው። የሮይተርስ ቡድን አባል ከሆኑት ስድስት ሰዎች ውስጥ ሦስቱ ደህና መሆናቸውን ማረጋገጡንም የዜና ወኩሉ ጨምሮ ገልጿል።
ሮይተርስ በመግለጫው “የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን ለራያን ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች ማስተላለፍ እንፈልጋለን። ራያን ብዙ ጋዜጠኞቻችን በዓለም ዙሪያ ያሉ ክስተቶችን እንዲዘግቡ ረድቷል፡፡ በጣም እንናፈቀዋለን” ብሏል። መግለጫው አክሎ የዜና ተቋሙ ስለጥቃቱ፣ ከክራማቶርስክ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር ጭምር፣ ተጨማሪ መረጃዎችን እየፈለገ መሆኑን እና ለስራ ባልደረቦች እና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አብራርቷል።
የ38 አመቱ ኢቫንስ የቀድሞ የእንግሊዝ ወታደር የነበረ ሲሆን፣ እ.አ.አ ከ2022 ጀምሮ የሮይተርስ የደህንነት አማካሪ ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል። አስክሬኑ በሆቴሉ ፍርስራሽ ውስጥ መገኘቱንም የዩክሬን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ሮይተርስ ሚሳይሉ የተተኮሰው ከሩሲያ ስለመሆኑ ወይም ጥቃቱ ሆን ተብሎ ስለመፈጸሙ በገለልተኛ አካል አለማጣራቱን ገልጾ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትርም ስለጉዳዩ ተጠይቆ ምላሽ አለመስጠቱን አመልክቷል።
በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሚካሄደው ጦርነት እ.አ.አ በ2022 የካቲት ወር ላይ ከተጀመረ ወዲህ ጦርነቱን ሲዘግቡ የነበሩ 15 ጋዜጠኞች መገደላቸውን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጄ መረጃ ያመለክታል።