እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በፈረንሳይቷ ኒስ ከተማ በተጠናቀቀው 111ኛ ጊዜ ቱር ደ ፍራንስ፣ ስሎቫንያዊ ታዴ ፓጋቻ አንደኛ ኾኖ ሲያሸንፍ፣ ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢኒያም ግርማይ ደግሞ
በሽምጥ (ስፕሪንት) አጠቃላይ ነጥብ፣ ዓለም አቀፉን የብስክሌት ውድድር በማሸነፍ፣ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ኾኗል።
ቤልጅየማዊው ሮሜኮ ኢቫንፓል በወጣቶች የነጭ ማልያ ተሸላሚ ሲኾን፣ በዳገት ውድድር ደግሞ ኢኳዶራዊው ደራዊ ሪቻርድ ካራፕስ ኣሸናፊ ሆኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኤርትራዊው የአረንጓዴ ማልያ አሸናፊ ቢንያም ግርማይ፣ ከኢንተርማርች ዋንቲ ክለብ ጋራ የነበረው ውል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 2028 መራዘሙ ታውቋል።
በሌላ በኩል ፣ የቤልጅየሙ ኢንተርማርች ዋንቲ ክለብ ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ የኾነው ቢኒያም ግርማይ፣ ብስክሌት መወዳደር የጀመረው ገና በልጅነቱ እንደነበር፣ አስመራ የሚገኘው የቀድሞው አሠልጣኙ ሶምሶን ሰሎሞን ያስታውሳል።
ቢኒያም ገና የ16 ዓመት አዳጊ ሳለ፣ ጎዳይፍ በተባለ ክለብ ውስጥ ውድድር ያደርግ እንደነበር የጠቀሰው ሶምሶን፣ በኋላም በጥረቱ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ይናገራል፡፡ ለዚኽ ደግሞ ወላጅ አባቱ፣ 250ሺሕ ናቅፋ/960ሺሕ ብር ገደማ/ ወጪ አድርገው የገዙለት ብስክሌት፣ ከፍ ባሉ ውድድሮች ለመሳተፍ እንዳስቻለው ይመሰክራል፡፡ “ያላቸውን አሟጠው ነበር ብስክሌቱን የገዙለት” ይላል የቀድሞ አሠልጣኙ፡፡
ቢኒያም እና የቀድሞ አሠልጣኙ የተገናኙት፣ አስቤኮ በተባለ ክለብ ውስጥ ነበር፡፡ ቢኒያም ብዙም ሳይቆይ የኤርትራን ብሔራዊ ቡድን በመቀላቀሉ የሠልጣኝ – አሠልጣኝ ግንኙነታቸው መጠናከሩን ሶምሶን ያስታውሳል፤ የተለየ ችሎታ እንዳለውም እማኝነቱን ሰጥቷል።
አስመራ የሚገኘው ዘጋቢያችን ብርሃነ በርኸ፣ ከቢኒያም ግርማይ አሠልጣኝ ጋራ ያደረገውን ቆይታ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።