አዲስ የተመረጡት የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚንስትር ኬይር ስታርመር የሌበር ፓርቲያቸው የሀገሪቱን ምርጫ ውድድር በከፍተኛ ድምጽ በማሸነፍ ፣ የወግ አጥባቂው ፓርቲ የ14 ዓመታት የበላይነት በቋጨ ማግስት ፣ የመጀመሪያ ሙሉ ቀን ኃላፊነታቸውን የካቢኔያቸውን ስብሰባ በመምራት ጀምረዋል።
አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በንጉስ ቻርለስ ሶስተኛ ከተረጋገጠ እና ሰንደቅ ዓላማ ባነገበው ህዝብ እና የሌበር ፓርቲ ለውጥ አቀናቃኞች ሆታ አቀባበል ከተደረገላቸው በኃላ ስትራመር ” የለውጥ ስራ በአስቸኳይ ይጀመራል !” ብለዋል።ብሪታኒያን ዳግም በመገንባት ረገድ ጥርጣሬ ሊኖር እንደማይገባም አክለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመን የመጀመሪያ ንግግራቸው በመንግስታቸው 5 ቁልፍ ተልዕኮዎች ዙሪያ አጽንኦት የሰጡት የ61 ዓመቱ ስታርመር ፣ መንግስታዊውን የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ፣ መልሶ ለማቋቋም ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ ድንበሮች እና ጎዳናዎችን ለማረጋገጥ ቃል ገብተዋል።
አዲሱ መንግስታቸው የተቀዛቀዘ ኢኮኖሚ ፣ ደካማ የህዝብ አገልግሎት እና ለዓመታት በቆየው የኑሮ ውድነት የተንገላቱ ቤተሰቦች ጉዳይ ከባድ ፈተና እንደሚሆኑበት ተነግሯል።
ሀገርን መለወጥ ቀላል አለመሆኑን ፣ ከዓለም ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ የተናገሩት ስትራመር ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህ በእንዲህ እያለ የዓለም ሀገራት መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የደስታ መልዕክታቸውን ማድረስ ይዘዋል።
ስታርመር ከዩኤስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት “በዩናይትድ ኪንግደም እና በዩ ናይትድ ስቴትስ መካከል ስላለው ልዩ ግንኙነት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት እና ለበለጠ የኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን የተጣጣመ ፍላጎት ተወያይተዋል” ሲል ከለንደን የወጣው መግለጫ አመላክቷል።
በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪን አነጋግረዋል(AFP)።