ቪኦኤ የፈረንሳይኛና የባምባራ ቋንቋ ሥርጭቶቹን ለሁለት ሣምንታት እንዲያቆም፣ የዌብሳይትና የማኅበራዊ መገናኛ ገፆቹን ተደራሽነት እንዲቀንስና የቡርኪናቤ ጦር በሲቪሎች ላይ እየፈፀመ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ረገጣ በተመለከተ በሚያወጣቸው ዘገባዎች ላይ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ለማድረግ የቡርኪና ፋሶ መንግሥት ያወጣው ትዕዛዝ ያሳሰበው መሆኑን የአሜሪካ ድምፅ አስታወቀ።
የቪኦኤ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጆን ሊፕማን ዛሬ በሰጡት መግለጫ “ቪኦኤ ስለ ቡርኪና ፋሶ በሚያቀርባቸው ዘገባዎች የሚተማመን ሲሆን በዚያች ሀገር ውስጥ ያሉ ክስተቶችን ሙሉ በሙሉና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መሸፈኑን ይቀጥላል” ብለዋል።
ሊፕማን አክለውም “የአሜሪካ ድምፅ ትክክለኛ፣ ሚዛናዊና ሁሉን አቀፍ የጋዜጠኝነት መርኆችን በጥብቅ የሚከተል በመሆኑ የቡርኪና ፋሶ መንግሥት ይህን አሳሳቢ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነው እንጠይቃለን” ብለዋል።
ሊፕማን “ዓለም ከአንድ ሣምንት በኋላ የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለማክበር በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት ነፃ የዜናና የመረጃ ፍሰትን ለመገደብ የተወሰደው ይህ እርምጃ ‘ነፃ ፕሬስ ዋጋ አለው’ ከሚለው የቪኦኤ ቋሚ መሪ ቃል በስተጀርባ ላለው እውነታ ሌላ ማሳያ ነው” ሲሉ አክለዋል።
እኤአ በ2020 ዓ.ም. በወጣ መረጃ መሠረት ቪኦኤ በቡርኪናፋሶ የሚያደርገው ሣምንታዊ ተደራሽነት 14.3 ከመቶ ነው።