በአሪዞና የግዛቲቱ የዲሞክራቲክ ፓርቲው ዓባላት በሥራ ላይ ያለውንና ፅንስ ማስወረድን የሚከለክለውን ሕግ ለመሻር ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ፣ ከሪፐብሊካኑ ዓባላት በኩል ድጋፍ ባለማግኘታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
በአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት በ1864 የወጣው ሕግ፣ ሁሉንም ዓይነት በሚባል ደረጃ ውርጃን ይከለክላል።
የግዛቲቱ ዲሞክራቶች በመጪው ኅዳር በሚደረገው ምርጫ በጉዳዩ ላይ ድምፅ እንዲሰጥበት ሙከራ በማድረግ ላይ ናቸው።
“የአሪዞና ሕዝብ ሆይ፣ በእንጀራ አባቷ የተደፈረች የ12 ዓመት ልጅ እንድትወልድ መገደድ አለባት ካልክ ሪፐብሊካኖችን ምረጥ” ሲሉ ተደምጠዋል የግዛቲቱ የሕግ መወሰኛ ም/ቤት ዓባል የሆኑት ዲሞክራቱ ኦስካር ዴ ሎስ ሳንቶሥ።
ዲሞክራቷ አገረ ገዥ ኬቲ ሃብስ በበኩላቸው፣ “በ27 ወንዶች በ1864 የተፃፈ ነው” ያሉትና “በአሪዞና የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን ሕይወት መቆጣጠር የለበትም” ያሉትን ሕግ ምክር ቤቱ እንዲሽር መጠየቃቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።