በአሜሪካ ኒው ጀርሲ ግዛት፣ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ የስደተኞች እና የጉምሩክ ኅይል (አይስ) ባደረገው አፈሳ የመኖሪያ ፈቃድ ከሌላቸው ግለሰቦች በተጨማሪ አንድ የቀድሞ ወታደርን ጨምሮ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ነዋሪዎች መያዙን የከተማዋ ከንቲባ አስታውቀዋል።
ከኒው ዮርክ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ኑወርክ ከተማ ስደተኞችን የሚቀበል ፖሊሲ ስታራምድ የቆይች ሲሆን፣ ባለፈው ሰኞ ወደ ሥልጣን ተመልሰው የመጡት ዶናልድ ትረምፕ ሰነድ አልባ ስደተኞች ተይዘው ከሃገሪቱ እንዲወጡ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት የፊዴራል ኅይሎች በከተማዋ በሚገኙ የሥራና የንግድ ሥፍራዎች አሰሳ አካሂደዋል።
ትረምፕ በሰጡት ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ፣ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ለመያዝ የሚደረገውን ጥረት ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ባለሥልጣናትን እንደሚቀጡ አስታውቀዋል።
በኑወርክ በተካሄደው አፈሳ የፌዴራል ኅይሎች የመያዢያ ትዕዛዝ እንዳሊያዙ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል። በዘመቻው የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎችንም መያዛቸው ታውቋል።
“ከተያዙት አንዱ የአሜሪካ የቀድሞ ወታደር ሲሆን፣ ያቀረበውን ወታደራዊ ሰነዶች የፌዴራል ኅይሎች በጥርጣሬ በማየታቸው ክብሩ ተነክቷል” ሲሉ የከተማዋ ከንቲባ የሆኑት ራስ ባራካ ተናግረዋል።
የአይስ ቃል አቀባይ በአወጣው መግለጫ፣ ኅይሎቹ አሰሳ በሚያደርጉበት ወቅት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችል አመልክቶ፣ ያላቸውን ሰንድ እንዲያቀርቡ ሊጠይቁ እንደሚችሉ፣ በኑወርክ ያጋጠመውም ይህ ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።
አይስ ሁኔታውን እየመረመረ እንደሆነም የቃል አቀባዩ መግለጫ ጨምሮ አመልክቷል።
“አፈሳው የአሜሪካ ሕገ መንግሥትን የሚጥስ ነው” ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል። “ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሽብር ሲፈፀምባቸው ኑወርክ ዝም ብላ አትመለከትም” ሲሉም አክለዋል።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ለቪት በ X ማኅበራዊ መድረክ ላይ እንዳስታወቁት፣ የትረምፕ አስተዳደር ትላንት ሐሙስ 538 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማድረጉንና “ሁሉም ሕገ ወጥ ፍልሰተኞችና ወንጀለኞች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
ስደተኞች አሜሪካ ከተወለዱት ዜጎች በላይ ወንጀል እንደማያፈጽሙ በርካታ የምሁራን እና ሌሎች የምርምር ተቋማት ጥናቶች እንደሚያመለክቱ የሮይተርስ ዘገባ ጠቁሟል።