ወደፊት ለአፍጋኒስተን የሚሠጥ የገንዘብ ድጋፍ፣ በሥልጣን ላይ የሚገኙት የታሊባን መሪዎች በሃገሪቱ የሚገኙትን የአሜሪካ ጦር መሣሪያዎች በመመለሳቸው ላይ እንደሚወሰን ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ አስታውቀዋል።
ትረምፕ ይህን ያስታወቁት ከትላንት በስቲያ ለደጋፊዎቻቸው በተዘጋጀ ሥነ ሥርዐት ላይ በአደረጉት ንግግር ነው።
የባይደን አስተዳደር በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላርና የጦር መሣሪያዎችን ጠላት ብለው ለጠሩት ወገን ሰጥቷል ያሉት ትረምፕ፣ የታሊባን መሪዎች የአሜሪካን የጦር መሣሪያዎችን የማይመልሱ ከኾነ የገንዘብ ርዳታ እንደማይደረግ አስታውቀዋል።
እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 2021 አሜሪካ በጥድፊያ ከአሜሪካ ስትወጣ 7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የጦር መሣሪያ ጥላ እንደወጣች የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ትረምፕ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ብለው የጠቀሱት ገንዘብ ለተመድ እና መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የሚሰጥ መኾኑን ሪፖርቶች አመልክተዋል። ለዚህም አሜሪካ ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንዳዋጣች ጠቁመዋል።