ከግብፅ፣ ቃጣር፣ አሜሪካ እና እስራኤል የተውጣጡ አደራዳሪዎች በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ “ቴክኒካዊ” ያሉትን መላ ለመሻት ካይሮ ላይ ዛሬ ተገናኝተዋል። ስምምነቱ ከዕሁድ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን እንደሚጠበቅ መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በዛሬው ስብሰባ ላይ ወደ ጋዛ በቀን 600 ዕርዳታ የጫኑ መኪኖች እንዲገቡ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ዕርዳታ የጫኑ ከባድ መኪናዎች በግብጽ ድንበር በኩል በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል።
የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔም ስምምነቱን ለማጽደቅ ዛሬ እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል። ካቢኔው የሚያጸድቀው ከሆነም በጋዛ ድብደባውና ጦርነቱ ቆሞ፣ ታጋቾች የሚለቀቁበት ሁኔታ ይመቻቻል ተብሏል።
ለረዥም ጊዜ ይጠበቅ የነበረው የእስራኤል እና የሐማስ የተኩስ ማቆም ስምምነት ጦርነቱን የሚያቆመው ከሆነ፣ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ወደ መኖሪያቸው ለመመልስ እንደጓጉ ተመልክቷል። ፍልስጤማውያኑ ወደ መኖሪያቸው የሚመለሱ ቢሆን እንኳ፣ አብዛኞቹ ምንም የቀረ ንብረት እንደማይኖራቸው፣ መልሶ ግንባታ ቢያስቡም የማይቻል እንደሆነ ተነግሯል። የእስራኤል ድብደባ በርካታ መንደሮችን ወደ አመድነት ቀይሯል።