በፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር የዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው ያገለገሉት ተሰናባቹ ጄክ ሱሊቫን፤ መጭው የትራምፕ አስተዳደር ጆ ባይደን አስጀምረውት ቻይናን እና ሰሜን ኮሪያን በመዋጋት ረገድ መልካም ደረጃ ላይ ያለውን የኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና ስልታዊ ወዳጅነት እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።
ጄክ ሱሊቫን አርብ ዕለት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ “ለትራምፕ አስተዳደር እያልን ያለው ነገር፤ አሜሪካ በቀጠናው ያላት አቋም በሚያስደንቅ ሁኔታ እጅግ ጠንካራ ነው” በማለት ከአሜሪካ ድምጽ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። አያይዘውም “ከኢንዶ-ፓሲፊክ ቀጠና ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ለውጥ ከማድረግ ይልቅ ስልታዊ ግንኙነቱን ማጠናከር የበለጠ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል” ብለዋል። “ነገር ግን መጪው ቡድን ምን እንደሚያደርግ አላውቅም።” ሲሉም አክለዋል።
ከባይደን አስተዳደር ኢንዶ-ፓሲፊክ ቀጠናን በተመለክተ ዋና ስልታዊ መሃንዲሶች መካከል አንዱ የሆኑት ጄክ ሱሊቫን፤ ቀጠናውን በተመለከተ የፕሬዝዳንት ባይደን አካሄድ “በትልቅ መንገድ ውጤታማ እየሆነ ነው” በማለት ከዚህ አካሄድ መራቅ ግን “አደጋን ያመጣል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይሁን እንጂ ጄክ ሱሊቫን የባይደን አስተዳደር የኮሪያን ባሕረ ገብ መሬት ከኒውክሌር ነጻ ማድረጉ ላይ እምብዛም መሻሻል እንዳላሳየ አምነዋል።
ትራምፕ ቅድሚያ አሜሪካ ወይም ‹‹አሜሪካ ፈርስት›› በሚሰኘው ካቢኔያቸው ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸውን ሁለት ታዋቂ የቻይና ተችዎችን በሃላፊነት አጭተዋል። የመጀመሪያው ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ሲሆኑ፤ የትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፀሐፊ እና ተወካይ ማይክ ዋልትዝ ደግሞ በትራምፕ አስተዳደር የጄክ ሱሊቫን ተተኪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።