በትግራይ ክልል የጤና ባለሞያዎች ፍልሰት እየጨመረ ነው፤ ያለው የክልሉ የጤና ባለሞያዎች ማኅበር፣ በየወሩ ከ80 በላይ የጤና ባለሞያዎች ክልሉን ለቀው እየሔዱና በክልሉ ውስጥም የሥራ ዘርፍ እየቀየሩ ናቸው፤ ሲል አስታውቋል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሥሓ አሸብር ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ በክልሉ ቀጥሏል ያሉት የፖለቲካ አለመረጋጋትና የኢኮኖሚ ችግር ለጤና ባለሞያዎቹ ፍልሰት መጨመር ምክንያት መኾኑን ጠቅሰዋል። በፕሪቶርያ ከተፈረመው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት በኋላ በአንድ ዓመት ውስጥ፣ ከ900 በላይ የጤና ባለሞያዎች የትግራይ ክልልን ለቅቀው ሔደዋል እንዲሁም ዘርፍ ቀይረዋል፤ ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
እንደ ዶክተር ፍሥሓ፣ ባለፈው ዓመት ማኅበሩ ከሌሎች ተቋማት ጋራ በመቀናጀት ባካሔደው ጥናት፦ 86 ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ 186 ጠቅላላ ሒኪሞች እና ከ500 በላይ በጤና ኬላ የሚሠሩ ባለሞያዎች፣ ከክልሉ የጤና ዘርፍ እንደወጡ መረጋገጡን ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ በበኩሉ፣ የጤና ባለሞያዎች በክልሉ የሚቆዩበትን ዕድል ለማመቻቸት የሚያስችል ውሳኔ ለመወሰን ጥናት እየተካሔደ መኾኑን ገልጿል። በአንጻሩ ማኅበሩ፣ የባለሞያዎቹ ፍልሰት፣ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክቷል። ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።