የቀድሞ የግሪክ ጠቅላይ ሚንስትር እና ሀገራቸው ወደ አውሮፓ የጋራ መገበያያ ገንዘብ እንድትቀላቀል ያደረጉት ኮስታስ ሲሚቲስ በ88 አመታቸው መመሞታቸውን የሃገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
በሙያቸው የስነህንጻ ባለሙያ የሆኑት ኮስታስ ሲሚቲስ የሶሻሊስት ፓሶክ ፓርቲ መስራችም ናቸው፡፡
ግሪክንም እአአ ከጥር 1996 እስከ 2004 ድረስ ለስምንት አመታት በጠቅላይሚንስትርነት መርተዋል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ረዥሙ የስልጣን የቆይታ ጊዜ የነበራቸው መሪም አድርጓቸዋል፡፡
ግሪክ የአውሮፓ ህብረትን እአአ በ 2001 እንድትቀላቀል ከማድረጋቸው በተጨማሪ ትልቅ የመሰረተ ልማት ግንባታ መርሃ ግብር በማካሄድ ሃገራቸው እአአ በ2004 የተካሄደውን የኦሊምፒክ ውድድርን እንድታዘጋጅ በማስቻላቸው ይታወሳሉ ። ቆጵሮስ የአውሮፓ ህብረትን በዚሁ አመት እንድትቀላቀልም ድጋፍ ማድረጋቸውም ይነሳል፡፡