ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጥፋተኛ በተባሉበት “አፍ ማስያዣ” ገንዘብ መክፈል ክስ ውሳኔ ለማስተላለፍ ጉዳዩን የያዙት ዳኛ በትናንትናው ዕለት ቀጠሮ ሰጥተዋል። ያልተጠበቀ እንደሆነ በተነገረለት የዳኛው እርምጃ መሰረት ፣ ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ ከሚመለሱበት ቀን 10 ቀናት አስቀድሞ -በአውሮፓዊያኑ ጥር 10 ቀን ውሳኔው ይፋ ይደረጋል። የቅጣት ውሳኔው ግን እስርን እንደማይጨምር ተመላክቷል ።
የዳኛው ውሳኔ ትራምፕ በወንጀሎች የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸው ስልጣን የተረከቡ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ያደርጋቸዋል።
የትራምፕን ችሎት የመሩት ዳኛ ሁዋን ኤም ሜርካን በፅሁፍ ባሰፈሩት ሀተታ፣ የቀድሞውን እና የወደፊቱን ፕሬዝደንት ሁኔታዎችን ያገናዘበ ውሳኔ እንደሚተላለፍባቸው አመላክተዋል ። በዚህም መሰረት ጉዳዩ ያለ እስራት፣ የገንዘብ ቅጣት ወይም አመክሮ ጊዜ ይዘጋል።
ሜርካን ፣ ፕሬዚደንታዊ ያለመከሰስ መብትን እንዲሁም ወደ ዋይት ሀውስ የመመለሻቸው ጊዜ መቃረቡን በመጥቀስ ውሳኔው ውድቅ እንዲደረግ ትራምፕ ያደረጉትን ግፊት አልተቀበሉም።
ዳኛው በትራምፕ ላይ ውሳኔ ከማስተላለፍ የሚከለክላቸው የህግ አግባብ እንደሌለ ገልጸው ጥር 20 ቀን ቃለ መሃላ ከመፈጸሙ በፊት ትራምፕ ላይ ውሳኔውን ማስተላለፍ “ግዴታ ነው” ብለዋል ።
የፍትህ መሻቶች የሚፈጸሙት “ይህ ጉዳእ የመጨረሻው እልባት ሲያገኝ ብቻ ነው” ሲሉ ሜርካን ጽፈዋል።
ትራምፕ በአውሮፓዊያኑ ግንቦት ወር 34 የንግድ መዝገቦችን በማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል።በአውሮፓዊያኑ 2016 የትራምፕ የመጀመሪያ የምረጡኝ ዘመቻ የመጨረሻ ሳምንታት ውስጥ ለወሲብ ፊልም ተዋናይቷ ስቶርሚ ዳኒልስ የተከፈለውን ገንዘብ ለመደበቅ ያለሙት ጥረቶችም በእነዚህ ጥፋቶች ውስጥ ተካተዋል።
ለስቶርሚ ዳኔልስ ክፍያዎቹ የተፈጸሙት ከባለትዳሩ ትራምፕ ጋር ከዓመታት በፊት ስጋዊ ግንኙነት እንደነበራቸው ለሕዝብ እንዳያሳውቁ ለማድረግ ነው።ትራምፕ ታሪኩ ሀሰተኛ እና ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል።
የመከላከያ ጠበቆች እና ዐቃቤ ህግ ጉዳዩን ዕጣ ፋንታ በተመለከተ አቋማቸውን ይፋ እስኪያደርጉ ድረስ፣ከህዳር 5 ምርጫ በኋላ፣ ሜርካን ሂደቱን አቁመው የቅጣት ውሳኔውን ላልተወሰነ ጊዜ አራዝመውት ነበረ።
የትራምፕ ጠበቆች መርካን መዝገቡን እንዲዘጉት ጠይቀዋል። ይህ ካልሆነ ጉዳዩ በተመራጩ ፕሬዝደንት ሀገሪቱን የመምራት አቅም ላይ ኢ-ህገመንግስታዊ “ሁከት” እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ዐቃቤነ ህጎች በበኩላቸው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ሊስተናገዱበት የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን ተቀብለው ፣ የጥፋተኝነት ውሳኔው ግን እንዳይለወጥ ተከራክረዋል።
ትራምፕ የስልጣን ዘመናቸው እስኪያበቃ ድረስ ጉዳዩ በይደር እንዲቆይ ወይም እስር የማይኖረው ቅጣት እንዲተላለፍባቸው ማረጋገጫ መስጠትን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮች ተጠቁመዋል።