በኬንያ እየጨመረ የመጣው የመንግሥት ተቃዋሚዎች ታፍኖ መሰወር እጅግ እንዳሳሰባቸው የመብት ቡድኖች፣ የሕግ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞች በመግለጽ ላይ ናቸው።
ቢሊ ምዋንጊ የተባለ የ24 ዓመት ወጣት ባለፈው ሳምንት በተሰወረባት ኢምቡ በተሰኘች ከተማ ተቃውሞ ተካሂዷል።
ባለፈው ሰኔ እና ሐምሌ በፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት ላይ በአብዛኛው በወጣቶች የተመራ ተቃውሞ ከተደረገ ወዲህ፣ የሃገሪቱ የፀጥታ ኃይሉች “በርካታ ተቃዋሚዎችን በሕገ ወጥ መንገድ አፍነው አግተዋል” የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል።
በተለይም ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶን በኢንተርኔት ላይ የሚተቹ ወጣቶች በመሰወር ላይ መሆናቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
ፖሊስ በጉዳዩ እጁ እንደሌለበት ቢያስታውቅም፣ የመብት አቀንቃኞች ግን ፖሊስ የተሰወሩትን ሰዎች በተመለከተ ለምን ምርመራ እንደማያደርግ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
ፖሊስ እጁ ከሌለበት ምርመራ አድርጎ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ሕግ ፊት ያቅርብ ሲል የኬንያ የሕግ ማኅበር ጠይቋል።
የመብት ቡድኑ ሂዩማን ራይትስ ዎች በበኩሉ ያደረጋቸው ምርመራዎች ከበርካታ የፀጥታ አካላት ወደ ተውጣጣ ቡድን እንደሚጠቁሙ አመልክቷል።
የቀድሞ ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩትና የተቃውሞ አያያዞችን በተመለከተ ከዊሊያም ሩቶ ጋራ ባለመስማማታቸው ከሥልጣን የተወገዱት ሪጋቲ ጋቻጉዋ፣ “ከአፈናው ጀርባ አንድ ድብቅ ቡድን አለ” ሲሉ ዛሬ ዓርብ ክስ አሰምተዋል።