እስራኤል ጋዛ ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት አንድ ሆስፒታል አቅራቢያ የነበሩ አምስት ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች ተገድለዋል ሲል የፍልስጤማውያኑ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል ሠራዊት በበኩሉ ኢላማ የተደረጉት የሐማስ አጋር የሆነው ‘እስላማዊ ጂሃድ’ የተሰኘው ቡድን አባላት ናቸው ብሏል። ቡድኑ ከሁለት ዓመታት በፊት እስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የጋዛው ጦርነት መቆስቆሱ ይታወቃል።
ጋዜጠኞቹ ‘ኩድስ ኒውስ ኔትወርክ’ ለተሰኘ ሚዲያ ይሠሩ እንደነበር ተቋሙ አስታውቋል።
ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ሲፒጄ ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ 130 ፍልስጤማዊያን ጋዜጠኞች መገደላቸውን አስታውቋል። እስራኤል ከሠራዊቱ ጋራ አብረው ከሚጓዙ ጋዜጠኞች ውጪ ሌሎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ አትፈቅድም።
እስራኤል በጋዛ የሚሠሩ ስድስት የአል ጃዚራ ጋዜጠኞችን ‘ነውጠኞች ናቸው’ በሚል አግዷል። መሠረቱን በቃጣር ያደረገው አል ጃዚራ ውንጀላውን ውድቅ በማድረግ ሲቪል ተጎጂዎች ላይ ያተኮሩትን ዘገባዎቹን እስራኤል ለማፈን በመሞከር ላይ ነች ሲል ክስ አሰምቷል።
በሌላ በኩል አንድ ተጠባባቂ ወታደሯ ዛሬ ጋዛ ውስጥ መገደሉን እስራኤል አስታውቃለች፡፡ እስራኤል በምድር ጋዛን ማጥቃት ከጀመረችበት ከአንድ ዓመት ወዲህ 389 ወታደሮቿ እንደተገደሉ አስታውቃለች፡፡
የፍልስጤማውያኑ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ እስራኤል በጋዛ በምታካሂደው ጦርነት እስከ አሁን 45 ሺሕ ፍልስጤማውያን እንደተገደሉ ያስታውቃል።