መጭው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የከፍተኛ ባለሃብቶች ሽርክና ስራ አስኪያጅ የሆኑትን ስኮት ቢስኔት የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት እንዲሆኑ መምረጣቸውን አስታውቀዋል።
የ62 ዓመቱ ቢስኔት ከጎርጎርሳውያኑ 1991 አንስቶ በቢሊየኔሩ ጆርጅ ሶሮስ የሽርክ ተቋም እና በሌሎች የሽርክና ተቋማት ውስጥ ሲሠሩ መቆየታቸው ተገልጿል። ሹመታቸው ከተረጋገጠም የዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያው ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ ግምጃቤት ሃላፊ ይሆናሉ። ቢሴንት የዋጋ ጉድለትን በመቆጣጠር የታወቁ ሲሆኑ የሀገሪቱ የብሔራዊ ብድር መጠን ለመቀነስ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
ቢሊዬነሩ ቢስኔት ቀድሞ የዴሞክራት ፓርቲ ቀንደኛ ደጋፊ የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ የትራምፕ ጥብቅ ደጋፊ ናቸው።
ቢስኔት በነሀሴ ወር ላይ ከብሉምበርግ የንግድ ዜና ተቋም ጋር ባደርጉት ቆይታ “ይህ ምርጫ ዩናይትድ ስቴትስ እንደ አውሮፓ የሶሻሊስት ዴሞክራሲ ከመሆኗ በፊት፤ ከገባችበት የዕዳ ተራራ የምንወጣበት የመጨረሻው እድል ነው።” በማለት ተናግረዋል።
ቢስኔት ትራምፕ በመጭው የሥልጣን ዘመናቸው ሊያደርጓቸው ያቀዷቸው የግብር ቅነሳዎች እና ቻይና ላይ ያነጣጠረ የታሪፍ ጭማሬን እንደሚደግፉም አስታውቀዋል።
ትራምፕ ባወጡት መግለጫም “ስኮት እጅግ በዓለም ላይ ግንባር ቀደም የሆኑ የጆኦፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት ስልት እና ኢንቨስተሮች ጉዳይ የከበሩ ናቸው” በማለት አሞካሽተዋቸዋል።