ከኮሪደር ልማት ጋራ በተያያዘ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ዛሬ ጠዋት ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል አቶ ሰዒድ አሊ፣ ዛሬ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ መታሰራቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር፣ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ “ግለሰቡ ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳ በኋላ፣ ዛሬ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ ከመኖርያ ቤታቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው በፖሊስ ኮሚሽኑ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል ” ብለዋል።
አክለውም፣ “ጉዳዩ በምርመራ ላይ ያለ በመኾኑ ዝርዝር ሁኔታውን ከዚኽ በላይ ለመግለጽ እንቸገራለን። የምርመራ ሥራው ከተጠናቀቀ ለሚዲያም ለሕዝብም እናሳውቃለን” ብለዋል።
የአቶ ሰዒድን ያለመከሰስ መብት መነሳት በተመለከተ፣ የምክር ቤቱ የፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ ለምክር ቤቱ በጹሑፍ ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ፣ አቶ አቶ ሰዒድ አሊ በሙስና ወንጀል በመጠርጠራቸው የወንጀል ምርመራ መዝገብ በዐቃቤ ሕግ ተከፍቶባቸው እንደነበር አስታውቀዋል።
በዚኹ በንባብ በቀረበውና በከተማው አስተዳደር መገናኛ ብዙኃን ላይ በተላለፈው የውሳኔ ሐሳብ፣ አቶ ሰኢድ ከማል፣ የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በነበሩበት ወቅት የኮሪደር ልማቱን ምክንያት በማድረግ፣ አኹን በእስር ላይ ከሚገኙ አራት የልደታ ክፍለ ከተማ ሠራተኞችና ከግል ባለሀብት ጋራ በመመሳጠር የመንግሥት ሀብትን ለግል ጥቅም እንዲውል አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው የወንጀል ምርመራ ሲደረግባቸው መቆየቱ ተገልጿል።
ፍትሕ ሚኒስቴር በሚኒስትሯ ፊርማ በተጻፈ ደብዳቤ የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የጠየቁበትን ደብዳቤ ኮሚቴው በጥልቀት መመልከቱን ሰብሳቢው ለምክር ቤቱ በንባብ አሰምተዋል።
በተጨማሪም ኮሚቴው የወንጀል ምርመራ መዝገቡን ከመረመረና፣ ከዐቃቤ ሕግ ጋራ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ፣ የምክር ቤት አባሉን የሕግ ከለላ ለማንሳት የሚያስችል በቂ አመላካች ኹኔታ አለ ብሎ በማመኑ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡን ገልጿል።
በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ መሰረትም የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብት ተነስቷል። ከውሳኔው በኋላ የምክር ቤት አባሉን ለማግኘት ጥረት ስናደርግ የቆየን ቢኾንም፣ በኋላ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከፖሊስ ለማወቅ ችለናል።