የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኑክሌር ቁጥጥር ተቋም ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ በሚቀጥለው ረቡዕ ኢራንን እንደሚጎበኙ ፣ በማግስቱም ከኢራን ባለስልጣናት ጋር ምክክር እንደሚጀምሩ የመንግስት ዜና አውታሮች ዘግበዋል።
የአለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቋም ሃላፊ አከራካሪ በሆነው የኑክሌር መርሐ ግብር ዙሪያ ለመወያየት በመጪዎቹ ቀናት ወደ ኢራን ሊያቀኑ እንደሚችሉ ፤ ከተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋርም በትብብር ለመስራት እንደሚጠብቁ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።
ቴህራን ከተቋሙ መርማሪ ቡድን የተላኩ የዩራኒያም ማበልጸግ ባለሙያዎችን መከልከሏ ፣ለዓመታት ባልተገለጹ ስፍራዎች የተገኙ የዩራኒየም ናሙናዎችን ምንጭ ለመግለጽ አለመስማማቷን ተከትሎ በተቋሙ ፣ በኢራን እና በምዕራብ ኃይላት መካከል ለረጅም ጊዜያት የቆዩ ችግሮች ተፈጥረዋል።
የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የአውሮፓዊያኑ የ2015ቱን፣ ኢራን የዩራኒየም ማብለጸግ እንቅስቃሴዋን እንደትቀንስ ከዓለም ኃያላን ጋር የገባችውን ስምምምነት በ2019 መሰረዛቸውን ተከትሎ ፣ ሀገሪቱ የኑክሌር እንቅስቃሴዋን አጠናክራለች ።
ቴህራን አቶሚክ ቦምብ ለመስራት ወደ ሚያስፈልገው 90 በመቶ የተጠጋ ፣60 በመቶ የንጥርነት አቅም ላይ የደረሰ ዩራኒየም እያበለጸገች መሆኑ ተሰምቷል ። በዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ተቋም መሰረት ሀገሪቱ የማበልጸግ ሂደቷን ከቀጠለች አራት ያህል የኑክሌር ቦምቦችን ለማምረት የሚያስችል ከበቂ ከፍ ያለ የበለጸገ ዩራኒየም ይኖራታል።
ኢራን ለሲቪል ሃይል ፍጆታ ብቻ ዩራኒየምን እያበለፀገች መሆኑን በመግለጽ የኒውክሌር ቦምብ ፍላጎት እንደሌላት ስታስተባብል ቆይታለች( ዘገባው የሮይተርስ ነው )።