በፊሊፒንስ “ትራሚ” የሚል ስያሜ በተሰጠው ከባድ አውሎ ንፋስ እና ዝናብ ባስከተለው አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 110 ደርሷል ሲሉ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ዛሬ እሁድ ተናገሩ ።
እስካሁን 42 የሚሆኑ ሰዎች ደብዛቸው እንደጠፋ ሲሆን የነፍስ አድን ሠራተኞች ፍለጋቸውን ቀጥለዋል፡፡
ባላፈው ሀሙስ እኤአ ጥቅምት 24 ፊሊፒንስን የመታው ትራሚ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ እና ቀያቸው አፈናቅሏል፡፡
ፊሊፒንስን ደቁሶ ወደ ቬትናም የገሠገሠው ትራሚ በማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል ዛሬ እሁድ ከባድ ዝናብ እንዲሁም በሰዓት 70 ኪሎሜትሮች የሚፈጥን ነፋስ ማስተከተሉ ተነግሯል፡፡
የትራሚ ከባዱ አውሎ ነፋስ፣ ቬትናም ከመድረሱ በፊት፣ ባለሥልጣናት የጀልባና የባህር ላይ እንቅስቃሴዎችን በማገድ ፣ 25ሺ ሰዎችም አካባቢያቸውን ለቀው እንዲቆዩ ማድረጋቸው ተመልክቷል፡፡
የአየር ትንበያ ባለሥልጣናት፣ በአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ሳቢያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእስያ ፓስፊክ ክልል የሚታዩ አውሎ ነፋሶች ከባህር ላይ ወደ ምድር ዳርቻ ተጠናክረው እየተጠጉ መንፈስ መያዛቸውና በየብስ ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸው በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡