ሶማሌ ክልል ውስጥ በተቃዋሚ ፓርቲነት የሚታወቀው፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብግ) በቅርቡ በክልሉ የአጀንዳ ልየታ ማጥናቀቁን ባስታወቀው፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው፣ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ አነሳ።
የኮሚሽኑ የተሳታፊዎች መረጣ በክልሉ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና ተጽዕኖ ሥር የወደቀ መኾኑን ፓርቲው በማኅበራዊ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መስፍን አርአያ፣ ተቋማቸው ግጭት ያለባቸውን ክልሎች ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ምክክሩን ለማካሄድ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የቀረበው ወቀሳ አስተባብለዋል።
በሌላ በኩል የፓርቲውን ስጋት የተጋሩት ዋና መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገው፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሃይለማርያም፣ እንዲህ ዐይነት የገለልተኝነት ጥያቄ ሲነሳ የመጀመሪያ አለመኾኑን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ አሳታፊ መኾን እንደሚገባው መክረዋል።