የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ዛሬ ቅዳሜ ዩጋንዳ ካምፓላ ገብተዋል። የአሁኑ ጉብኝታቸው በሶማሊያ ጸጥታ በሚያስከብሩ አራት ሀገራት ከሚያደርጉት የመጀመሪያው ነው።
ፕሬዝዳንቱ በካምፓላ ከዩጋንዳው አቻቸው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በጋራ ጉዳዮች፣ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ሽግግር አትሚስ ዙሪያ እና ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋትን በተመለከተ እንደሚወያዩ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ቤተመንግስት መግለጫ አስታውቋል።
ሀሰን ሼክ መሃሙድ በቀጣይ በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ አባል ሀገራት ወደ ሆኑትን ብሩንዲ፣ ኬኒያ እና ጅቡቲን ይጓዛሉ። የሶማሊያ ፕሬዘዳንት ቃል አቀባይ አብዱልቃድር ዲጌ ለአሜሪካ ድምጽ አፍሪካ ቀንድ ፕሬዘዳንቱ ኢትዮጵያን አይጎበኙም ሲሉ ተናግረዋል።
በሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ጸጥታ ለማስከበር የተሰማሩ ቢሆንም ነገርግን በጎርጎርሳዊያኑ 2024 መግቢያ ላይ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው አጨቃጫቂ ውል ሶማሊያን ሉዓላዊነቴን ጥሳለች በሚል አስቆጥቷታል።
የኢትዮጵያ ሰራዊት በፊታችን ታህሳስ ሙሉ ለሙሉ ከሶማሊያ ለቆ የሚወጣ ሲሆን ሁለት የሶማሊያ ባለስልጣናት ምንጮች ግብጽ በሶማሊያ የአፍሪካ ቀንድ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧን አረጋግጠዋል። የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አብዱልቃድር ዲጌ በሶማሊያ ቀጣዩ የሰላም አስከባሪ ማን እንደሚሆን መታየቱ ገና እንደቀጠለ ነው ብለዋል።