በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ አምባሰል ወረዳ፣ ግሸን አምባ በሚገኙ ሁለት ባንኮች ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በፈፀሙት ዘረፋ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ ወስደዋል ሲሉ የሁለት ባንኮች የአካባቢው ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች ተናግረዋል።
በግሸን አካባቢ የሚገኙት የአቢሲኒያ እና ጸደይ ባንኮች ቅርንጫፎች ሥራ አስኪያጆች ደሴ ላይ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ዘረፋው የተፈጸመው ባለፈው መስከረም 25 ቀን 2017 ዓም ነው በማለት አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ወሎ አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ለአካባቢው ማኅበረሰብና ወደስፍራው ለሚመጡ ምእመናን አገልግሎት እንዲሰጡ የተከፈቱ ባሏቸው ባንኮች ላይ ተፈጸመ ያሉትን ዘረፋ አውግዘዋል፡፡
የባንኮቹ ዋና መስሪያ ቤቶች ግን፣ የቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች መሆናቸውን የገለፁት ኃላፊዎች ይፋ ባደረጉት የዘረፋ ጉዳይ ላይ ያወጡት ይፋ መግለጫ የለም።
የአሜሪካን ድምፅ ሁኔታውን ከዋና መሥሪያ ቤቶቹ ለማጣራት ያደረገው ጥረትም ለጊዜው አልተሳካም።