በምዕራብ ወለጋ ዞን በሚገኙት ቤጊ እና ቆንዳላ ወረዳዎች፣ እንደዚሁም በቄለም ወለጋ ዞን፣ ሳጆ ወላሊ ወረዳ በመንግሥት ታጣቂዎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል፣ ባገረሸው ግጭት፣ “ባለፉት ሦስት ቀናት ቢያንስ ስድሰት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል” ሲሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
“ሰዎቹ የተገደሉት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ካፈገፈጉ በኋላ የመንግሥት ኀይሎች በወሰዱት እርርምጃ ነው “ያሉት ነዋሪዎቹ ድርጊቱን ኮንነዋል።
በጉዳዩ ላይ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና በየደረጃው ካሉ ባለስልጣናት ምላሽ ለማገኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ከዚህ በፊት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኀይሉ አዱኛ ለተመሳሳይ ውንጀላ በሰጡት ምላሽ፣ “የመንግሥት ኀይሎች ሲቪል ሰዎችን ዒላማ አያደርጉም፤” በማለት አስተባብለዋል።
“ለታጣቂው ቡድን የሎጅስቲክስ ድጋፍ የሚያደርጉና መረጃ የሚሰጡ ሰዎች ይያዛሉ” ሲሉ አክለው የገለጹት አቶ ኀይሉ፣ ጉዳያቸው የሚጣራው “ሕግን በተከተለ መንገድ” መኾኑን ተናግረዋል።