ወታደራዊ አመራሩ የተገደለው እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት ከሌሎች አስራ ስድስት ተዋጊዎቹ ጋር መሆኑን ሂዝቦላ ዛሬ አስታውቋል፡፡
እስራኤል ትላንት በሊባኖስ ዋና ከተማ ደቡባዊ ዳርቻዎች ላይ ባካሄደችው ጥቃት የሂዝቦላህ ‘ኢሊት ራድዋን ፎርስ” በመባል የሚታወቀውን ወታደራዊ ሃይል መሪ ኢብራሂም አቂል እና ሌሎች በርካታ አዛዦች መገደሏን አስታውቃለች።
ለሰላሳ ሰባት ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው በግኑኝነት መሳሪያዎች ላይ ከደረሰው ጥቃት በሁላ ወታደራዊ አመራሮቹ የተገደሉበት በኢራን ይደገፋል የሚባለው ሂዝቦላ ወታደራዊ አደረጃጀቱ ላይ አዳዲስ ጥያቄዎች እየተነሱበት ይገኛል፡፡
ሂዝቦላህ የጋዛ ጦርነት ከጀመረበት ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስካሁን ድረስ በእስራኤል ላይ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት መርቷል ያለውን አህመድ መሀሙድ ዋህቢን ሁለተኛው አዛዥ አድርጎ መሰየሙን አስታውቋል፡፡
ሂዝቦላ መገደሉን ያረጋገጠው ኢብራሂም አቂል እ.ኤ.አ. በ 1983 ቤይሩት በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ላይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ በዩናይትድ ስቴትስ ሲፈለግ የነበረ ሰው ነው፡፡