እየተሸኘ ያለው አዲስ ዓመት ምን ትቶ አልፏል መጭውስ ምን ተስፋ ሰንቋል?
ለአዲሱ ዓመት “ሁሉም ሰው ሊመኘው የሚገባው ነገር ሰላም ብቻ ነው” ይላሉ በአማራ ክልል የባህርዳር ነዋሪዋ ወ/ሮ ወይንሸት ገመቹ፡፡
ከቤንሻንጉል ክልል የተፈናቀሉትና በሂደቱም ባለቤታቸውን በሞት ያጡት ወ/ሮ ወይንሸት ገመቹ አራት ልጆቻቸውን በህይወት ለማሰንበት እየተጣጣሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ወ/ሮ ወይንሸት ስለመጭው ዓመት አዲስ ተስፋም ሆነ ውጥን ባይኖራቸውም አሮጌውን ዓመት የሚሸኙት “በህይወት መቆየት በመቻለቸው ብቻ አምላካቸውን በማምሰገን” መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የ2016 ዓመት ምህረትን በተደባለቁ ስሜቶች ያሳለፉ መሆናቸውን የገለጹልን ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ያለው የኑሮ ውድነትና ከሁሉም በላይ የሰላም ሁኔት እስካልተረጋጠ ድረስ ከመጭው የ2017 ዓመት አዲስ ነገር እንደማይጠብቁ ነግረውናል፡፡
የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው በትግራይ በአማራ በኦሮምያ ክልልና አዲስ አበባ የሚገኙ ነዋሪዎች አዲሱን ዓመት የሚያከብሩት ከቀድሞው ባነሰ ድምቀት እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችችን አካሂዳለች፣ ይህንም ተከትሎ የመጡ የኑሮ ውድነቶች አሉ” የሚሉት በኦሮምያ ክልል የአዳማ ነዋሪ አቶ ኤዳኦ አብዲ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያን ምርቶች ወደ ውጭ በመላክ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ኤዳኦ “በተለይ በቀይ ባህር አካባቢ በየመን ሁቲ አማጽያን የተስተጓጎለው የንግድ መርከቦች ስምሪት አቅጣጫውን በመቀየሩ ለኑሮ ውድነት መባባስ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ማድረጉን” ይናገራሉ፡፡
“አምና ግማሽ ኪሎ ስጋ እንገዛ ከነበርን ዘንድሮ ወደ ሩብ ኪሎ እንወርዳለን” ያሉት በኦሮምያ ክልል የምስራቅ ወለጋ ነዋሪ አቶ ዋቅጅራ የአዲሱ ዓመት ትልቁና ቀዳሚው ምኞታችን “ሰላም ነው” ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባዋ ነዋሪ ወ/ሮ መሰረት ገዙ የሁለት ልጆች እናት ናቸው፡፡ እንኳን ለሚቀጥለው ዓመት ለማሰብ “የእለት ኑሮን ማሸነፍ ራሱ እየከበደ ሁሉን ነገር ትተን ተቀምጠናል” ይላሉ፡፡
የገበያውን ውድነት ሲገልጹም “አንድ እንቁላል 11 ብር ነው፣ ዶሮ ከ1300 ብር በላይ ነው፣ ጤፍ በኪሎ 155 ብር ነው ፣ በርበሬ አንዷ ኪሎ 4 ብር ከ50 ያውም ከቅመም ውጭ… ነው” እያሉ ይዘረዝራሉ፡፡
የ11 እና የ ሰባት ዓመት ህጻናት ለሆኑት ሁለት ልጆቻቸው “ለበዓል አዲስ ልብስ እና አዲስ ጫማ ይገዛላቸው ነበር” ያሉት መሰረት “አሁን በዚህ ዓመት ግን አልገዛሁላቸውም ከአቅሜ በላይ ነው” ብለዋል፡፡
በዚያ ላይ “በዓል መጣ ሲባል እንደወትሮው በዓል ማክበሩን ሳይሆን በሰላም ውለህ ማደርህን ነው የምታሰበው” ሲሉም አክለዋል መሰረት፡፡
መረጋጋት በጎደለው የአማራ ክልል አንድ ልጃቸውና ወንድማቸው በፖሊስና የመንግሥት ኃይሎች እንደተገደሉባቸው የተናገሩት የባህር ዳር ነዋሪ ወ/ሮ ወርቄ ከበደ “አዲሱ ዓመት ብዙም ደስ አይልም” ይላሉ፡፡
“በአካባቢው ያለው ሁኔታ ደስ አይልም፤ ከቤት ስንወጣ በየቦታው ፍተሻ ነው፣ የኑሮ ውድነቱ፣ የገበያው ሁኔታ አለ፣ የሰው ሞት አለ፣ ብዙ ነገር ስላለ ብዙ ደስታ ባይኖርም መቸም እንደ አዲስ ዓመት እንቀበለዋለን፤ ተስፋ አንቆርጥም፤ የእግዚአብሄርን ምህረት እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡
“መስቀልና እንቁጣጣሽ የምንለው አዲስ ዓመት ትግራይ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚከበሩ በዓላት ናቸው” ያሉን ደግሞ በትግራይ ክልል የተንቤን ነዋሪ አቶ ካሳሁን ወ/ጊዮርጊስ ናቸው፡፡
“ህዝቡ አሁን በተስፋ ነው የሚኖረው፡፡ ሰላም ስላለው ደስ ይለዋል፤ ይህን ሰላም ተጠቅሞ የተሻለ ሰላም ይመጣልኛል ብሎ ተስፋ ያደርጋል፡፡” የሚሉት አቶ ካሳሁን፣ ክልሉ “በከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር፣ በከፍተኛ ማህበራዊ ችግር ውስጥ ነው፤ ቢሆንም በጦርነቱ ጊዜ ከነበረው ጊዜ የተሻለ ነው” ብለዋል፡፡
“ይሁን እንጂ ቋንቋ የማይገኝለት፣ ሊገለጥ የማይችል፣ የነገውን ነገር ደማቅ በሆነ ብርሃን እንዳይታይ የሚጋርድ ነገር ትግራይ ውስጥ አለ” ሲሉም አክለዋል፡፡
አቶ ካሳሁን እንደሚሉት ለዚህ ምክንያቱ “ትልቅ የፖለቲካ ፍትጊያ መኖሩ” ነው፡፡
የትግራይ ህዝብ “ካለፈው መከራው እየተማረ መምጣቱንና፣ ብስለት ማሳየቱን” በመግለጽ “የተሻለ ጊዜ ለማምጣት በተስፋ ላይ ይገኛል” ሲሉም መጭውን ዘመን በዚያው ቀና መንፈስ እንደሚጠባበቅ አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡