የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ካመላ ሄሪስ ለአሜሪካ ፕሬዝደንትነት እንዲወዳደሩ በፓርቲው መታጫተቸውን በይፋ ተቀበለዋል።
ካመላ ሄሪስ እጩ መሆናቸውን በይፋ የተቀበሉት በቺካጎ ከተማ ለአራት ቀናት ሲደረግ በነበረው የፓርቲያቸው ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ሐሙስ ምሽት ባሰሙት ንግግር ነው።
ስለ አስተዳደጋቸውና ስለ ወላጆቻቸው የተናገሩት ካመላ ሄሪስ፣ አስተዳደጋቸው አሁን ያሉበት ቦታ ለመድረሳቸው መሠረት እንደሆነ አስታውቀዋል። ቤተሰብና እምነት ሰዎችን ለመቅረጽ ሚና እንዳለው አውስተዋል። እናታቸውን “ፈር ቀዳጅ” ሲሉ የገለጹት ሄሪስ፣ አባታቸው ደግሞ “ፈሪ እንዳይሆኑ” አድረገው እንዳሳደጓቸው ተናግረዋል።
“የየትኛውም ፓርቲ አባል ይሁኑ፣ በሁሉም ሕዝቦች ስም፣ ….. በእናቴ ስም……… አብረውኝ ባደጉ አሜሪካውያን ስም፣ ጠንክረው በሚሰሩ ሰዎች ስም፣ በምድር ታላቅ በሆነችው ሃገር ታሪካቸው በሚጻፈው ሰዎች ሁሉ ስም ለፕሬዝደንትነት መታጨቴን እቀበላለሁ” ብለዋል ካመላ ሄሪስ።
የየትኛውም ፓርቲ አባል ይሁኑ፣ በሁሉም ሕዝቦች ስም፣ ….. በእናቴ ስም……… አብረውኝ ባደጉ አሜሪካውያን ስም፣ ጠንክረው በሚሰሩ ሰዎች ስም፣ በምድር ታላቅ በሆነችው ሃገር ታሪካቸው በሚጻፈው ሰዎች ሁሉ ስም ለፕሬዝደንትነት መታጨቴን እቀበላለሁ”
“ለሁሉም አሜሪካዊ ፕሬዝደንት እንደምሆን ቃል እገባለሁ” ሲሉም አክለዋል።
ካመላ ሄሪስ በአንድ ዋና ፓርቲ ለፕሬዝደንትነት ሲታጩ የመጀመሪያው ጥቁር እሲያ አሜሪካዊ ሴት ናቸው።
በውጪ ፖሊሲ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ከዩክሬን እና ከኔቶ ጎን እንደሚቆሙ አስታውቀዋል። በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲመጣ፣ በጋዛ የሚታየውን ሰቆቃ ለማስቆም ፣ፍልስጤማውያን ክብራቸው እንዲጠበቅ ከፕሬዝደንት ባይደን ጋራ እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።
“እስራኤል ራሷን የመከላከል መብቷን ሁሌም እደግፋለሁ። የመከላከል አቅም እንዲኖራትም ሁሌም አረጋግጣለሁ” ብለዋል።
ሄሪስ በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ፣ የመጀምሪያው ሴት የአሜሪካ ፕሬዝደንት ይሆናሉ።