የቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ዲሞክራቶች ለምርጫ ‘ፍልሚያው’ እንዲዘጋጁ አሳሰቡ፡፡
የቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ትላንት ማክሰኞ ምሽት በዲሞክራቲክ ፓርቲ ብሔራዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “ችቦው ወደ ካመላ ሄሪስ ቢተላለፍም” የዲሞክራቶች ሥራ ገና እንዳለተጠናቀቀ አስገንዝበዋል።
ቺካጎ ላይ እየተደረገ ባለው ጉባኤ በሁለተኛው ምሽት ዋና ተናጋሪ የነበሩት ኦባማ፣ በጥቅምት ወር መጨረሻ በሚደረገው ምርጫ አሜሪካኖች ድምጽ መስጠት እንዳለባቸውና እንዳይዘናጉ አሳስበዋል።
“እንዳትሳሳቱ፣ ትልቅ ፍልሚያ ይሆናል” ብለዋል ኦባማ። ያለው መነቃቃት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ እና ሰልፍ እንዳለ ሆኖ፣ “ለሁለት በተከፈለው ሃገር ምርጫው ተቀራራቢ ፉክክር የሚታይበት ነው” ብለዋል።
በዲሞክራቲክ ፓርቲው ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ኦባማ “ተስፋ ይሰማኛል” ሲሉም ተናግረዋል።
የጉባኤው ታዳሚዎች ለቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ፣ ‘የጀግና’ አቀባበል እንደተደረገላቸው የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል። ኦባማ በምላሹ፣ “መነቃቃትና ተስፋ” እንደሚሰማቸው ለታዳሚው ተናግረዋል። ካመላ ሄሪስ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝደነት እንዲሆኑም ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
“አሜሪካ ለእርሷ ያደረገላትን መልካም ነገር ሌሎችም እንዲያገኙ ሕይወቷን ሙሉ ስትጥር የኖረችን፤ የምትሰማችሁንና እና የምትረዳችሁን፤ በየቀኑ ለእናንተ የምትታገልን ግለሰብ ለመምረጥ ዕድሉ አለን” ሲሉ ተናግረዋል ኦባማ።
ጉባኤው ዛሬ ምሽትም የሚቀጥል ሲሆን፣ ለምክትል ፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት ቲም ዋልዝ፣ የቀድሞው ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን እና የቀድሞዋ የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ ንግግር እንደሚያደርጉ ፕሮግራም ተይዟል።