የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት፣ ዛሬ ኀሙስ ባካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ፣ በክልሉ ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት ምትክ ዐዲስ መሪዎችን መሾሙን፣ የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡ ምክር ቤቱ፣ ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር፣ ዶክተር ጋልዋክ ሮንን ደግሞ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል፡፡
የመሪነቱን ሥልጣን የተረከቡት ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ፣ በሥራቸው፥ ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ ቅድሚያ እንደሚሰጡ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡
በአመራር ለውጡ ላይ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡት፣ የጋምቤላ የኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ዴቪድ ሩዋች፣ “ዛሬ የተሾሙት መሪዎች፥ በቂ የትምህርት ዝግጅት እና ልምድ ያላቸው ስለኾኑ፣ የክልሉን የሰላም ችግር በመፍታት ረገድ ለውጥ ያመጣሉ” ብለዋል፡፡
አንድ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ዐዲሱ አመራር በብሔር ልዩነት ምክንያት ችግር ላይ የወደቀውን የክልሉን ሕዝብ አንድነት ለመመለስ እንዲሠራ ጠይቀዋል።