የመረጃ ጠለፋ እንደተደረገበት ያስታወቀው የቀድመው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚደንታዊ ዘመቻ ተቋም ፣ ቁልፍ የውስጥ ሰነዶቹን ከመስረቁ እና ከማሰራጨት ተግባር ጋር በተያያዘ ኢራንን ተወቃሽ አድርጓል ። ዘመቻው የኢራንን ተሳትፎ የሚያሳይ ማስረጃ አላቀረበም ። የአሁኑ ክስ የተሰማው ማይክሮሶፍት የውጭ አካላት በዘንድሮው የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ዘመቻዎች ውስጥ ጣልቃ ሊገቡ እንደሚችሉ ዝርዝር ሪፖርት ባቀረበ ማግስት ነው።
ተቋሙ ለማሳየነት ፣ ከተጠለፈ የቀድሞ ከፍተኛ አማካሪ ኢሜል አድራሻ ፣ በኢራን ጦር የስለላ ቡድን አማካኝነት በሰኔ ወር ለአንድ ፕሬዚደንታው የምርጫ ዘመቻ ከፍተኛ ባለስልጣን የተላከ “መጥለፊያ ቀመር ” ያዘለ ኢሜልን ጠቅሷል ።
የትራምፕ ዘመቻ ቃል አቀባይ ስቲቨን ቺዩንግ የአሁኑን ጠለፋ ፣” የአሜሪካ ጠላት የሆኑ የውጭ ምንጮች ” ያላቸው አካላት መፈጸማቸውን ተናግረዋል ። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደህነት ምክር ቤት ባተመው መግለጫ ፣ አግባብነት የሌላቸውን የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ” በላቀ ትኩረት ” እንደሚመለከት ገልጾ ፣በዩናይትድ ስቴትስ የዲሞክራሲ ተቋማት ላይ ያለውን እምነት ለማዳከም የሚሞክርን ማንኛውንም መንግስት ወይም አካል እንደሚያወግዝ ነገር ግን ጉዳዩ ወደ ፍትህ መስሪያ ቤት መተላለፉን አስታውቋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢራን ተልዕኮ ስለ ትራምፕ ዘመቻ ክስ ለቀረበለት ጥያቄ ፣ በተግባሩ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደሌለው አስተባብሏል።”በእንደዚህ አይነት ዘገባዎች ላይ ምንም አይነት እምነት የለንም ” ሲል ተልዖኮው ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግሯል። “የኢራን መንግስት በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውስጥ ጣልቃ የመግባት አላማም ሆነ ገፊ ምክንያት የለውም” ሲልም አክሏል ።
ሆኖም ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ እና ተሻግሮ ባሉ ጠላቶቿ ላይ ያነጣጠረ የጠለፋ ዘመቻ ታካሂዳለች በሚል ሲጠረጠር ቆይቷል።ቴህራን እ.ኤ.አ. በ2020 ታዋቂው አብዮታዊ ጠባቂ ጄኔራል ቃሲም ሱሌይማኒን የገደለውን ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ባዘዙት ትራምፕ ላይ የብቀላ እርምጃ እንደምትወስድ ለረጅም ጊዜ ስትዝት ቆይታለች(ዘገባው የሮይተርስ ነው)።