የሩሲያውን የፖለቲካ ተቃዋሚ ቦሪስ ኒምስቶቭን በመግደል የተፈረደበት ታምርላን ኧስከርካኖቭ በዩክሬኑ ጦርነት ሰራዊቱን ለመቀላቀል ኮንትራት ከፈረመ በኋላ ከእስር መለቀቁን የሀገሪቱ መንግሥት ዜና አገልግሎቶች ዛሬ ቅዳሜ ዘገቡ፡፡
ኔምስቶቭ የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ዋነኛ ተቃዋሚ እና በቀድሞ ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲን አስተዳደር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡
እኤአ በ2015 በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ውስጥ ክሬምሊን አጠገብ በሚገኘው ድልድይ አቅራቢያ በእግራቸው ሲንቀሳቀሱ በተተኮሰባቸው ጥይት ኔምስቶቭ እንደተገደሉም ተገልጿል፡፡
የሩሲያ ፍርድ ቤት ከግድያው ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን አምስት ሰዎች እኤአ በ2017 ከ11 እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስር ፈርዶባቸው እንደነበር ተዘግቧል፡፡
ከእነዚህ መካከል ታምርላን ኧስከርካኖቭ ተባባሪ ሆኖ በመገኘቱ 14 ዓመት ተፈርዶበት ነበር፡፡
አሁን ከሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር ወደ ዩክሬን ዘምቶ ለመዋጋት በመስማማቱ ይቅርታ ተደርጎለታል ሲል የሩሲያ የዜና አገልግሎት ታስን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሌሎች እስረኞ ኮንትራንቱን ለመፈረም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከእስር አለመፈታታቸው ተዘግቧል፡፡
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ እስረኞች ከሠራዊቱ ጋር ለመቀላቀል ፈቃደኛ በመሆን መስራታቸው ሲነገር ፣ የሩሲያ መከላከያ እስኪረከበው ድረስ ዋግነር የተሰኘው ቅጥረኛው የሩሲያ ተዋጊ ቡድን ዋነኛው መልማይ እንደነበር ተመልክቷል፡፡