ደቡብ ሱዳን፣ የናይል ተፋሰስ ባለፈው ሳምንት አጽድቃለች፡፡ ዐዲሷ የተፋሰሱ ሀገር የወሰደችውን ርምጃ፣ የጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “ታሪካዊ” ሲሉ አድንቀዋል፡፡
በሌላ መጠሪያው “የኢንቴቤ ስምምነት” እየተባለ የሚታወቀው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነት፣ በደቡብ ሱዳን መጽደቁ፣ ስምምነቱ በተፋሰሱ ሀገራት ተግባራዊ ሊኾን የሚችልበትን በቂ ድጋፍ የሚያስገኝ ነው፡፡
በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፣ ደቡብ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር ኾና የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱን መፈረሟ፣ ስምምነቱ “ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝና ወደ ተግባር እንዲሸጋገር የሚያስችል ነው፤” ብለዋል፡፡
ዐሥራ አንዱም የተፋሰሱ ሀገራት የሚጋሩትን የናይል ወንዝ፣ “ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ለግብጽ እና ለሱዳን ብቻ ያከፋፍላሉ፤” በሚል የሚተቹትን የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በመሻር በዐዲስ ለመተካት ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡
የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱ ሐሳብ አመንጪዎች እና ግንባር ቀደም ተዋናዮች ከኾኑት ሰባት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት አንዷ የኾነችው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ “የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነት በደቡብ ሱዳን መጽደቁ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ነው፤” ሲሉ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በማኅበራዊ የትስስር ገጾቻቸው አወድሰዋል፡፡
የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነት በደቡብ ሱዳን መጽደቁ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ነው፤”
ስምምነቱ ለ11 ዓመታት ከዘለቀ ውይይት በኋላ፣ በ2002 ዓ.ም. (በአውሮፓውያኑ 2010) ግንቦት ወር ላይ በኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ዑጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ኬንያ ሲፈረም፣ ብሩንዲ በቀጣዩ ዓመት ስድስተኛ ሀገር ኾና ፈርማለች፡፡ ከእነዚኽ ሀገራት መካከል ከኬንያ በቀር አምስቱ ስምምነቱን በየአገሮቻቸው ሲያጸድቁ፣ ደቡብ ሱዳን ስድስተኛዋ የስምምነቱ አጽዳቂ ሀገር ኾናለች፡፡
የናይል ተፋሰስ የውኃ ምንጭ የኾኑት የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት፣ የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱ፥ “ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም” የሚለውን መርሕ የሚያሟላ መኾን እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ ስምምነቱ፥ “የውኃ ደኅንነታችንንና ታሪካዊ ድርሻችንን ማረጋገጥ አለበት፤” የሚል አቋም ያላቸው ግብጽ እና ሱዳን በበኩላቸው፣ እስከ አሁን ስምምነቱን አልፈረሙም፡፡
ደቡብ ሱዳን ስድስተኛ ሀገር በመኾን ስምምነቱን ማጽደቋን ተከትሎ፣ ከሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እስከ አሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም፡፡
ስምምነቱ በደቡብ ሱዳን መጽደቁን፣ “ዲፕሎማሲያዊ እመርታ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው፣ ይህም “በናይል ተፋሰስ ቀጣናዊ ትብብር ለማድረግ ባለን የጋራ ምኞት ጉልሕ ርምጃ ነው፤” ብለዋል።
ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡት በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፣ የደቡብ ሱዳን ውሳኔ፣ ከ11ዱ የተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ የስምምነቱን አጽዳቂዎች ቁጥር ወደ ስድስት በማድረስ ወደ ተፈጻሚነት እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል፡፡ ይህም፣ ግብጽ እና ሱዳን፣ በቅኝ ግዛት ስምምነቶች መሠረት አለን የሚሉትን ታሪካዊ የውኃ መብት ጥያቄ የሚያስቀር እንደኾነ ያስረዳሉ፡፡
በአውሮፓውያኑ 1929፣ በግብጽ እና በብሪታኒያ መካከል የተፈረመው ስምምነት፣ ከቅኝ ግዛት ስምምነቶች አንዱ ነው፡፡ በናይል(ዓባይ) ወንዝ እና በተፋሰሶቹ ላይ የሚገነቡ ማንኛውም ግንባታዎች፣ “ያለግብጽ ይኹንታ እንደማይከናወኑ ይደነግጋል፤” ይላሉ ፕር. ያዕቆብ።
የትብብር ማኅቀፍ ስምምነቱ በአንጻሩ፣ የናይል ተፋሰስ ሀገራት እያንዳንዳቸው በየግዛታቸው ውስጥ የናይል ወንዝን ውኃ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በኾነ መንገድ የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይገልጻል፡፡ ስምምነቱ፣ በስድስት ሀገራት
በተፈረመባቸውና በአምስቱ ከጸደቀ በኋላ ባሉ የተለያዩ ጊዜያት የግብጽ ባለሥልጣናት በሰጧቸው አስተያየቶች፣ ምንም እንኳን አገሪቱ የስምምነቱን በርካታ አንቀጾች ብትቀበልም፣ “ለአወዛጋቢ ጉዳዮች እልባት የሚሰጥ አይደለም በማለት” በተቃውሞዋ መቀጠሏን ገልጸዋል፡፡
ይኹን እንጂ፣ ስምምነቱ በስድስት ሀገራት መፈረሙን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መኾኑን የሚገልጹት የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ ፕር. ያዕቆብ አርሳኖ፣ ግብጽ እና ሱዳን አለመፈረማቸው ወደ ኋላ ሊመልሰው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት፣ አባል ሀገራት፣ በናይል ተፋሰስ ውኃ ላይ በሚሠሯቸው ግንባታዎች ምክንያት ቅሬታዎች ቢነሡ፣ ስምምነቱ መጽደቁን ተከትሎ በሚቋቋም የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን እልባት እንደሚሰጠውም አስረድተዋል፡፡
በትብብር ማኅቀፉ ስምምነት ላይ፣ በላይኛው የተፋሰሱ ሰባት ሀገራት እና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ግብጽ እና ሱዳን መካከል መግባባት ካልተደረሰባቸው ነጥቦች መካከል፣ “በሌሎች የናይል ተፋሰስ ሀገራት የውኃ ደኅንነት ላይ ጉልሕ ተጽእኖ አለማሳደር” የሚለው አንቀጽ 14(ለ) ዋናው ነው፡፡
ይህ አንቀጽ “በሌሎች የተፋሰስ ሀገራት የውኃ ደኅንነት፣ እንዲሁም የአሁን አጠቃቀምና መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር” በሚል እንዲተካ ግብጽ ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡
የናይል የሚኒስትሮች ምክር ቤት በግንቦት ወር 2001 ዓ.ም. በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኪንሻሳ ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በአንቀጽ 14(ለ) ላይ የተመለከተው ጉዳይ፣ በናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን እልባት እንዲሰጠው ወስኗል፡፡