ሁለት የእስላማዊ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ባለስልጣናት ከተጀመረ ዘጠኝ ወራት የሞሉትን የጋዛ ጦርነት ለማስቆም ቁልፍ አጋር የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ ያቀረበችውን ሀሳብ መቀበሉን እና ተኩስ ለማቆም የእስራኤልን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ዛሬ እሁድ አስታውቀዋል።
ከሁለቱ የሀማስ ባለስልጣናት መካከል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንደኛው ባለስልጣን “ምላሻችንን ለአስታራቂዎቹ ሰጥተናል አሁን የወራሪዎቹን ምላሽ ለመስማት እየጠበቅን ነው” ብለዋል።
የፍልስጤምን ሰርጥ በተመለከተ ሦስት-ደረጃዎች ያሉት ዕቅድ በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቀረበ ሲሆን ካታር እና ግብፅ እያሸማገሉ ነው። እቅዱ ጦርነቱን ለማስቆም እና በሀማስ ተይዘው የነበሩትን 120 የሚጠጉ የእስራኤል ታጋቾችን ነፃ ለማውጣት ያለመ ነው።
ጋዛን የተቆጣጠረው ሀማስ ቀድሞ፤ ‘ስምምነት ከመፈረሙ በፊት እስራኤል በመጀመሪያ ለዘላቂ የተኩስ አቁም ቃል እንድትገባ’ አስቀምጦት የነበረውን ቁልፍ ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። በአንጻሩ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ሳምንታት ድርድሮች እንዲሳካ እንደሚጥር መናገሩን አንድ ማንነታቸው እንዳይገልጽ የጠየቁ የሀማስ ምንጭ በግል ውይይት መናገራቸውን ትላንት ቅዳሜ ሮይተርስ ዘግቧል።
ለሰላም ጥረቱ ቅርበት ያላቸው አንድ ሌላ የፍልስጤም ባለስልጣን ሀሳቡን እስራኤል ከተቀበለች ወደ ስምምነት ማዕቀፍ ሊያመራ እንደሚችል እና ጦርነቱን እንደሚያቆም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ድርድሩ በዚህ ሳምንት እንደሚቀጥል ቢናገሩም ዝርዝር የጊዜ ገደብ አልሰጡም።