በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ቀራኒዮ ከተማ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ የፋኖ ታጣቂዎች በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ፣ በደብረ ቀራኒዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ሰባት ሲቪሎች መገደላቸውን፣ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ እና በቦታው ነበርን ያሉ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ሟቾቹ፣ ከዕለቱ አንድ ቀን ቀድመው በሕይወት ለተለዩ መነኵሲት የመቃብር ጉድጓድ ሲቆፍሩ የነበሩ ስድስት እድርተኞች እና አንድ የአብነት ተማሪ መኾናቸውን፣ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ፣ በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና መቃብር ሲቆፍሩ በነበሩት ሟቾች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው፣ የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ማማሩ ዓይናበባ፣ እርሳቸው መልስ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አለባቸው ብርሃኑ፣ መረጃው ለኮሚሽኑ እንደደረሰውና ጉዳዩንም እያጣራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡