የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዘዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ ከዛሬ ቅዳሜ ሰኔ ስምንት እስከ ሰኔ 11/2016 ድረስ በአዲስ አበባ ቆይታ እንደሚያደርጉ የመንግስታቱ ቢሮ መግለጫ አስታውቋል።
ፕሬዘዳንቱ በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
በተመሳሳይ ፕሬዘዳንቱ አፍሪካ ህብረትንም እንደሚጎበኙ እና ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ሞኒክ ንሳንዛባጋናዋ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉም መግለጫው አክሎ አትቷል። በተጨማሪም ፕሬዘዳንቱ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ቢሮ ሃላፊ ክሌቨር ጋቴት ጋት ኮሚሽኑ በቀጠናዊ የልማት ጥረቶች ላይ ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና ለማቅረብ ይገናኛሉ ብሏል።
ፕሬዘዳንቱ እና ሉዑካቸው ተጨማሪ ተወካዮችን እና የተለያዩ የመንግስታቱ ድርጅት እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ቢሮ ሃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚኖራቸው ተገልጿል።