የየመን የሁቲ አማፅያን ሪፐር (MQ-9 Reaper) የተባለውን የአሜሪካዊ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ተኩሰው መጣላቸውን ትላንት አርብ አስታውቁ፡፡
አማፅያኑ ይህን ያስታወቁት የተጠቀሰውን ድሮን ስብርባሪ የሚመስሉ ነገሮችን የሚያሳዩ ምስሎች በኢንተርኔት ለሰዓታት ከተሰራጩ በኋላ ነው፡፡
ዛሬ ቅዳሜ ማለዳውም ላይ በቀይ ባህር ላይ የነበረ አንድ መርከብ ጥቃት የደረሰበት መሆኑን ታውቋል፡፡
ሁለቱ ክስተቶች የሁቲ አማፅያን በጋዛ ሰርጥ ያለውን የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት በመቃወም ከሚያደርጉት የቅርብ ጊዜ ጥቃቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ብ/ ጀነራል ያህያ ሳሬ እንደተናገሩት ድሮኑ የተመታው ባላፈው ሀሙስ ከምድር ወደ አየር በተወነጨፈ ሚሳዬል ነው፡፡
ቃል አቀባዩ ድሮኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና በተሰጠው የየመን መንግሥት በሚቆጣጠረው ማሪብ ግዛት ውስጥ “የጥቃት ርምጃዎችን” ሲወስድ የነበረው ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ከምድር በምሽት የተወነጨፈው ሚሳዬል ድሮኑን ሲመታ የሚያሳየው የኢንተርኔት ቪዲዮ ምስል “እግዚአብሄር ታላቅ ነው፣ ሞት ለአሜሪካ ሞት ለእስራኤል፣ ርግማን ለአይሁዶች፣ ድል ለኢስላም” በሚሉ መፈክሮች የታጀበ መሆኑም በአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ ተመልክቷል፡፡
የቪዲዮው ምስል የድሮኑ ስብርባሪዎች የሚመስሉና በእሳት የተቃጠሉትን አሳይቷል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ስለ ሁቲ መግለጫም ሆነ ከአሶሴይትድ ፕሬስ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው አስተያየት አለመኖሩን ዘግባው አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2014 ሁቲዎች የሀገሪቱን ሰሜናዊ እና ዋና ከተማዋን ሰነዓን ከተቆጣጠሩ በኋላ የአሜሪካ ጦር ከዚህ ቀደም ቢያንስ አምስት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በአማፅያኑ አጥቷል።
ሪፐር (Reaper) ወይም በአማርኛ ትርጉሙ አጫጅ የተባለው ድሮን 30 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን እስከ 50,000 ጫማ ከፍታ መብረር እና እስከ 24 ሰአታት አየር ላይ መቆየት የሚችል ነው፡፡