የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን የቪዛ አሰጣጥ ሂደት ለማጥበቅ መወሰኑን አስታወቀ፡፡
የኅብረቱ ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ የቪዛ አሰጣጥ ገደቡ “የኢትዮጵያ መንግሥት በህገ ወጥ መንገድ በኅብረቱ ሀገሮች የቆዩ ዜጎቹን ወደ ሀገራቸው በመመለስ ረገድ በቂ ትብብር ባለማሳየቱ” መሆኑን አስታውቋል፡፡
ኅብረቱ ይህን የወሰነው የአውሮፓ መንግሥታት በጦርነት ከሚታመሱ የአፍሪካ ሀገራት ብዙ ጊዜ በወንጀል በተደራጁ ቡድኖች አቀናባሪነት በአደገኛ ሁኔታ በሜዲትራኒያን ባህር በኩል አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞችን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እያደረጉ ባሉበት በዚህ ወቅት ነው።
“ይህ ውሳኔ የተሰጠው ኮሚሽኑ ባደረገው ግምገማ መሰረት ኢትዮጵያ በህገ-ወጥ መንገድ በአውሮፓ ህብረት ሀገሮች የሚቆዩትን ዜጎቿን በማስመለስ ረገድ የምታደርገው ትብብር በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ነው” ሲል የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤቱ ገልጿል።በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ ህግ አውጪዎች የተሻሻለውን የፍልሰት ስርዓት ማጽደቃቸው ይታወሳል።
ቀኝ አክራሪው ክንፍ በመጪው ሰኔ ወር ከሚካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ አስቀድሞ እያገኘ ያለውን ድጋፍ ለመቅረፍ የሚሻው የአህጉራዊው ህብረት ደጋፊ ወገን፣ የፍልሰት ሥርዓቱ መሻሻል ያለ ህጋዊ ሰነድ የሚመጡትን ፍልሰተኞች ቁጥር ይቀንሰዋል ብሎ ያምናል፡፡