በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ለታገተው ኤርትራዊ ሕፃን፣ 400ሺሕ ብር የማስለቀቂያ ቤዛ እንደተጠየቁ ወላጅ አባቱ ተናገሩ፡፡
በወረዳው በሚገኘው የዓለምዋጭ ስደተኞች መጠለያ የሚኖሩት የታጋቹ ሕፃን አባት አቶ መሐመድ ዑስማን፣ ልጃቸው ከታገተ ሁለት ሳምንት ማስቆጠሩን ገልጸው፣ የተጠየቁትን ገንዘብ ለማሰባሰብ ልመና ላይ መሰማራታቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በበኩሉ፣ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋራ በመኾን እያጣራን ነው፤ ብሏል፡፡
የስደተኞች መጠለያ ጣቢያው የሚገኝበት የጭላ ቀበሌ አስተዳደር ደግሞ፣ ጉዳዩን ፖሊስ እየተከታተለው እንዳለና ከእገታው ጋራ በተገናኘ የተያዘ ግለሰብም መኖሩን አስታውቋል፡፡
በዓለምዋጭ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሌሎች የኤርትራ ስደተኞችም፣ እገታን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጸጥታ ችግሮች እያጋጠሟቸው እንደኾነ አመልክተዋል፡፡
ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።