እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፈጣን የኮሌራ መመርመሪያ ባለፈው ዓርብ ለአገሮች መላክ መጀመሩን የዓለም የጤና ድርጅት እና አጋሮቹ አስታወቁ፡፡እየጨመረ የመጣውን ወረረሽኝ ለመዋጋት የየተያዘውን ጥረት እንደሚያጠናክር ተቋማቱ አመልክተዋል፡፡
ማላዊ ወረርሺኙን በፍጥነት ለመከታተል በታለመው ዓለም አቀፍ መርሐ ግብር የተላኩ ፈጠን መመርመሪያዎችን በመቀበል የመጀመሪያ ሆናለች፡፡
“በመጪዎቹ ወራት ለወረርሺኙ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ለሆኑ 14 ሀገራት በድምሩ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ መመርመሪያዎች ይላካሉ” ሲል የመንግሥታቱ ድርጅት ጤና ተቋም በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
“በሚቀጥሉት ሳምንታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከፋፈለውን ግዙፍ ቁጥር ያለው መመርመሪያ የሚረከቡት በኮሌራ ወረርሽኝ ክፉኛ የተጎዱትን እንደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ሶሪያ እና ዛምቢያ ያሉትን ይጨምራል” ሲል መግለጫው አመልክቷል።
መርሃ ግብሩን የጋቪ ክትባት ጥምረት የገንዘብ ድጋፍ እና ማስተባበሩን፣ የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት ድርጅት ዩኒሴፍ ደግሞ ግዥውን ይቆጣጠራል።
የዓለም ጤና ድርጅትም ከኮሌራ ቁጥጥር ግብረ ኃይል ጋር በመሆን ድጋፉን እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።
መርሃ ግብሩ ሀገራት የኮሌራ ወረርሽኙን በፍጥነት መለየት እና የሚሰጡትን ምላሾች በማሻሻል መደበኛ የክትትልና የምርመራ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ለማገዝ ያለመ መሆኑን ድርጅቶቹ ገልጸዋል።
የጋቪ መርሀ ግብር ኃላፊ ኦሬሊያ ንጉየን “በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሌራ ተያዦች ቁጥር በበርካታ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እየጨመረ በመሆኑ ዛሬ ይፋ የተደረገው የመመርመሪያ ድጋፍ በሽታውን በመዋጋት ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል” ብለዋል።
በተበከለ ምግብ ወይም ውሃ በሚተላለፍ ባክቴሪያ የሚጋባው ኮሌራ ተቅማጥ እና ትውከትን የሚያስከትል ሲሆን በተለይ ለታዳጊ ህፃናት አደገኛ ሊሆን ይችላል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበሽታው ተጋላጮች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል፡፡
እኤአ በ2022 በዓለም አቀፍ ደረጃ 473,000 መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት ዘገባ ያሳያል፡፡ ይህ ከቀደመው ዓመት በእጥፍ እንደሚበልጥ የተገመተ ሲሆን የተደረገው የናሙና ጥናት እንደሚያሳየው እኤአ በ2023 ለበሽታው የተጋለጡ ከ 700,000 ሰዎች በላይ ተመዝግበዋል።
በከፍተኛ ደረጃ በተዛመተው ወረርሽኝ ከተጎዱ አገሮች የሚቀርበው የክትባት ጥያቄ ባልተለመደ መልኩ ጨምሯል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፍ የሚሰጡ የኮሌራ ክትባቶች አቅርቦት እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በአስራ ስምንት እጥፍ ቢያድግም እየጨመረ ያለው ፍላጎት ዓለም አቀፍ እጥረት ፈጥሯል ሲል መግለጫው አመልክቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ወር እጥረቱን ለመቅረፍ “አፋጣኝ እርምጃ” እንዲወሰድ ሲጠየቅ “በዓለም አቀፍ የክትባት ክምችት ላይ ታይቶ የማያውቅ ጫና” ፈጥሯል ሲል አስጠንቅቋል።
በዓርቡ መግለጫ ላይ እንደተመለክተው ለድንገተኛ አጣዳፊ ወረርሽኝ ምላሾች የሚደረገው ዘመቻ የመከላከያ ክትባት ዘመቻዎች እንዲጓተቱ አስገድዷል።
የዩኒሴፍ አቅርቦት ክፍል ኃላፊ ሌይላ ፓካላ በመግለጫው ላይ “ምርመራዎች በሽታው የተከሰተባቸውን አዳዲስ ቦታዎችን በትክክል ለመለየት ይረዳሉ፣ አጋሮችም፣ የኮሌራ ክትባቶችን የተወሰኑ ጊዜ እና ቦታዎችን ለይተው እንዲሰጡ ያስችላቸዋል” ብለዋል፡፡