የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ፣ እስራኤል ጋዛ ውስጥ ጦርነት የምታከናውንበትን ሂደት ካላስተካከለች ፣ ሀገራቸው የፖሊሲ ለውጥ እንደምታደርግ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ ፣ እስራኤል ተጨማሪ እርዳታ ወደ ስፍራው እንዲገባ ተጨማሪ እርምጃ እንደ ወሰደች እና በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰባት የዓለም አቀፍ ረድኤት ሰራተኞችን ከገደለው የአየር ጥቃት ጋር በተያያዘ ሁለት የጦር ባለስልጣናቷን እንዳሰናበተች አስታወቀች ።
በአውሮፓዊያኑ ሚያዚያ 1 የደረሰውን ክስተት በተመለከተ ሲደረግ የቆየው ምርመራ መጠናቀቁን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ ፣ አንድ የብርጌድ አዛዥ እና ምክትላቸውን እንዳባረረ አስታውቋል ። ሌላ የብርጌድ አዛኝ ፣ የክፍለ ጦር አዛዥ እና የደቡባዊ እዝ ኃላፊ ደግሞ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አክሏል ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ፣ የጦር አመራሮች “ወርልድ ሴንትራል ኪችን ” በተሰኘው ተቋም አባላት የሚዘወሩ ሶስት የረድኤት መኪኖች ፣ የሀማስ ታጣቂዎች ተሸሽገውባቸዋል የሚል የተሳሳተ ዕምነት ውስጥ እንደነበሩም ገልጿል ።
ጥቃቶቹ የተፈጸሙት ፣ የኃይሉን መሰረታዊ የዘመቻ ደንቦች እና ትዕዛዝ በመጣስ እንደሆነም በመግለጫው ተመላክቷል ።
አርብ ዕለት ወደ ብራሰልስ ከመብረራቸው በፊት ፣ የአሜሪካ የውጭ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንተኒ ብሊንከን ሀገራቸው የእስራኤልን ጦር ኃይል ምርመራን በጥንቃቄ እየመረመረች እንደሆነ እና ከእስራኤል ባለስልጠናት እና ሰብዓዊ ተቋማት ጋር ተጨማሪ ንግግሮች እንደሚደረጉ ተናግረዋል ።
“እስራኤል ለክስተቱ ሙሉ ኃላፊነት መውሰዷ በእጅጉ አስፈላጊ ነው” ያሉት ብሊንከን ፣ ” ተመሳሳይ ነገር መቼም እንዳይፈጠር ፣ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ማረጋገጥ ፣ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው ብለዋል ”