መጋቢት 21/2016 (አዲስ ዋልታ) ግጭቶችን በንግግርና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፓርቲው ዝግጁ ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የፌዴራል ተቋማት የብልጽግና ፓርቲ አባላት ማጠቃለያ ኮንፈረንስ “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝደንት አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኮንፈረሱ የገጠሙንን ተግዳሮቶች በመገምገም በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የምንግባባበት ነው፡፡
ፓርቲው ባለፉት ግዜያት እንደሀገር ለደረሰባቸው ስኬቶች በዋናነት ሶስት ጉዳዮች መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በዚህም የኢትዮጵያን አቅም ለመለየትና ለመጠቀም የተደረገው ጥረት ቀዳሚው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ባሻጋር ለጥራት፣ ለፍጥነትና ለፈጠራ የተሰጠው ትኩረት እንዲሁም የፍትሃዊነት መርህን ተከትሎ መሰራቱ የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡
ግጭት ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮችን በንግግርና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፓርቲው ዝግጁ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ይህ ማለት ግን ሁሉም አካላት በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ተዘጋጅተዋል ማለት አይደልም ያሉት ምክትል ፕሬዝደንቱ ይህ ደግሞ ህግን በማስከበር ሰላምን የማስፈን ተግባር እንደሚከናወን አስገንዝበዋል፡፡
የመንግስትን ስልጣን በኃይል ለማግኘትና ለመያዝ የሚደረጉ ጥረቶች እንደማይሳኩ የገለጹት አደም ፋራህ ስልጣን በሀሳብ ልዕልና እና በህዝብ ይሁንታ ብቻ የሚገኝ መሆኑን የተረጋገጠባቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ለግጭቶች ሰላማዊ አማራጭ እንዲኖር ፣ የህግ የበላይነንትን ማረጋገጥ እንዲጠናከር፣ አካታች ብሄራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን አቅጣጫ ማስቀመጡንም አውስተዋል።
በሰለሞን በየነ