የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የፀጥታው ም/ቤት፣ ለእስልምና እምነት ተከታዮች ቅዱስ ወር በሆነው የረመዳን ወቅት በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ዛሬ ሰኞ ጠየቀ፡፡ የጸጥታ ምክር ቤቱ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ሲጠይቅ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።
ታጋቾች እንዲለቀቁም የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ አሜሪካ በድምፀ ተአቅቦ አልፋዋለች፡፡ ዛሬ የተላለፈው የውሳኔ ሃሳብ፣ ከግብፅ እና ከካታር ጋራ በመሆን የተኩስ ማቆም እንዲደረግ በማካሄድ ላይ ያለችውን ድርድር እንደሚጎዳ አሜሪካ አስታውቃለች፡፡
ባለፈው ወር በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ ማቆም የውሳኔ ሃሳብ ቻይናና እና ሩሲያ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን በመጠቀም ውድቅ አድርገውታል።
የዛሬው የውሳኔ ሃሳብ በ10 የተመረጡ የም/ቤቱ አባላት የቀረበ ሲሆን፣ ሩሲያ እና ቻይና እንዲሁም 22 አባላት ባሉት የዓረብ አገራት ቡድን እንደሚደገፍ ታውቋል።
የዓረብ አገራት ቡድኑ ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ፣ 15 አባላት ያሉት የፀጥታው ም/ቤት “በአንድነት እና በአስቸኳይ” የውሳኔ ሃሳቡን በማፅደቅ “ደም መፋሰሱን እንዲያቆም እና ሕይወትን እንዲታደግ” ጠይቀዋል።