ሩሲያ ለስድስት የአፍሪካ ሀገሮች በነጻ 200 ሺህ ቶን ዕህል መላኳን የግብርና ሚንስቴሯ ከትናንት በስተያ ማክሰኞ አስታወቀ፡፡
የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ሀገራቸው ዕህሉን እንደምትልክ ባለፈው ሐምሌ ወር ከአፍሪካ ሀገሮች መሪዎች ጋር ባደረጉት ጉባኤ ቃል ገብተው ነበር፡፡
ፑቲን ሩሲያ በነጻ ዕህል እንደምትልክ ቃል የገቡት ዩክሬን በጥቁር ባሕር ወደቦቿ በኩል ዕህል ወደ ውጪ እንድትልክ ሀገራቸው የፈቀደችበትን ስምምነት ሀገራቸው መሰረዟን ተከትሎ ነው፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን ግዙፍ የዕህል አቅርቦት ወደ ውጭ ላኪ ሀገሮች ሲሆኑ “የጥቁር ባሕር የዕህል አቅርቦት መርሐ ግብር” የሚል ስያሜ የሚታወቀው ስምምነት በዓለም ገበያ የዕህል ዋጋ እንዲቀንስ በማድረግ ረድቷል፡፡ የሩሲያው መሪ ግን ስምምነቱ “አቅርቦቱ በአንገብጋቢነት ለሚያስፈልጋቸው ሀገሮች ዕህል ለማድረስ አልቻለም” በማለት መከራከራቸው ይታወሳል፡፡ ማክሰኞ ዕለት ከክሬምሊን ቤተ መንግሥት በወጣው መግለጫ መሠረት የሩስያ የግብርና ሚኒስትር ዲሚትሪ ፓትሩሼቭ ለሶማሊያ እና ለማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ለእያንዳንዳቸው 50 ሺህ ቶን ዕህል እንደተላከ ፕሬዚደንት ፑቲንን አሳውቀዋቸዋል፡፡ ቀደም ሲል ለኤርትራ፣ ለማሊ፣ ለቡርኪና ፋሶ እና ለዚምባቡዌ እያንዳንዳቸው 25 ሺህ ቶን ዕህል እንደተላከ ተመልክቷል፡፡
በክሬምሊን ቤተ መንግሥቱ መግለጫ መሠረት ሩሲያ እአአ በ2023 – 2024 ባለው የግብርና ዓመት በጠቅላላው 70 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዕህል እንደምትልክ የሚጠበቅ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ይህም በገንዘብ 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚገመት መሆኑን እና በመጠኑም በቀደመው የግብርና ወቅት ከተላከው 66 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ዕህል እንደሚበልጥ ሚኒስትሩ ማመልከታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡