የዩክሬን ጦር በዶኔትስክ ግዛት ውስጥ ከምትገኘው አቭዲቪካ ለቆ እየወጣ መሆኑን ዛሬ አስታወቀ፡፡
በአንድ ቀን ውስጥ እስከ 30 የሚደርሱ የሩሲያ የከባድ መሣሪያ ድብደባዎች ጋር እየተጋፈጠ መሆኑን የጠቀሰው የዩክሬን ጦር ከስፍራው ለቆ መውጣቱ “ለሞስኮ የሚያስገኘው ስልታዊ ጥቀሜታ የለም” ብሏል።
የዩክሬን ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ሲርስኪ ርምጃው “የወታደሮችን ህይወት ለመጠበቅና ከከበባ ለማዳን” የተወሰደ ርምጃ መሆኑን በፌስቡኩ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡
የዩክሬን ደቡብ ዕዝ ጦር አዛዥ ኦሌክሳንደር ታርናቭስኪ የአቭዲቭካ የጦር ግንባር እስከ 1000 ኬሎሜትሮች በሚሸፍን ስፍራ የተዘረጋ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሰሞኑን በሰጧቸው መግለጫዎች ለዩክሬን የሚሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባላት ለዩክሬን በሚሰጠው ወታደራዊ የድጋፍ መጠን ላይ እስካሁን አልተስማሙ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለነስኪ ትናንት አርብ ከፈረንሳይ ጋር ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የወታደራዊ ደህንነት ትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ለ10 ዓመት ይቆያል በተባለው ስምምነት ፈረንሳይ የዩክሬንን ጦር ማሰልጠንን ጨምሮ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ዩክሬን የምትልክ ሲሆን በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት ውስጥ እስከ 3.2 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምትሰጥ ተመልክቷል፡፡
የሩሲያ ሚሳዬሎች የዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭን ያጠቁ መሆናቸው ሲነገር ሁሉም ሚሳዬሎች በዩክሬን አየር መከላከያ እየተመቱ መምከናቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡