ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ በጋዛ “ወንጀሎችን” መሥራታቸውን ከቀጠሉ የሜዲትራኒያን ባህር መተላለፊያ ሊዘጋ እንደሚችል የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ማስጠንቀቃቸውን የኢራን ሚዲያ ዘግቧል። ኢራን ባህሩን በምን መልኩ ልትዘጋ እንደምትችል ግን አልተገለጸም።
ኢራን ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ የሚገኘውን ሐማስ የምትደግፍ ሲሆን፣ እስራኤል ለሳምንታት በዘለቀ የቦምብ ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመግደል እና ሚሊየኖችን ቤት አልባ በማድረግ በጋዛ እየፈፀመች ነው ያለችውን ወንጀል፣ ዩናይትድ ስቴትስ ትደግፋለች ስትል ትከሳለች።
“በቅርቡ የሜዲትራኒያን ባህር፣ የጅብራልተር እና ሌሎች መተላለፊያ ወሽመጦች ይዘጋሉ” ሲሉ የአብዮቱ ዘብ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል መሐመድ ረዛ ናቅዲ መናገራቸው ተጠቅሷል።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ላለችው ጥቃት አፀፋ፣ ከኢራን ጋር ቁርኝት ያለው የየመን ሁቲ ቡድን ባለፈው ወር ቀይ ባህርን አቋርጠው በሚጓዙ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ቆይቷል። ይህም አንዳንድ የመርከብ ኩባንያዎች መስመራቸውን እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል።