በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የወሰደውብቸኛው የውጪ ኩባንያ ኢትዮ- ሊዝ፣ በኢትዮጵያ ያለውን የሥራ እንቅስቃሴ እንደሚያቋርጥ በትላንትናው ዕለት አስታወቀ።
ኢትዮ ሊዝ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ሥራውን እንዲያቋርጥ፣ ዋና መቀመጫውን በኒውዮርክ ካደረገው የኢትዮ ሊዝ ኩባንያ ባለቤት ‘አፍሪካን አሴት ፋይናንስ’ መመሪያ እንደተሰጠው አስታውቋል።
የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ለውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ክፍት ለማድረግ መንግሥቱ ያወጣውን የማሻሻያ እቅድ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ2012 ዓ.ም ፍቃድ የሰጠው ኢትዮ ሊዝ፣ በፋይናንሱ ዘርፍ በመሰማራት የመጀመሪያው የውጭ ኩባንያ ነው።
ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ዓመት በፊት ያወጣው መመሪያ፣ ድርጅቱ አዲስ የሊዝ ውል መዋዋል እንዳይችል ስላደረገው አገልግሎቱ ለማቋረጥ ምክኒያት እደኾነው ኢትዮ ሊዝ አስታውቋል።
ባንኩ ያወጣው ማሻሻያ ማንኛውም የሊዝ ስምምነቶች ቋሚ ክፍያዎች ከውጭ ምንዛሪ ይልቅ በኢትዮጵያ ብር እንዲሆን እና ውሉ በሚፈጸምበት ወቅት ባለው የምንዛሪ ተመን በብር እንዲከፈሉ ይወስኗል።
ከተባለው ማሻሻያ በተጨማሪም፣ የውጭ አገር የሊዝ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ብር እንዳይበደሩ የሚከለክል ሌላ መመሪያ፣ “የትኛውም የውጭ አገር የሊዝ ኩባንያ በኢትዮጵያ ሥራውን እንዳይሠራ አዳጋች ያደርጋል” ሲል አክሏል።
ኢትዮ ሊዝ እና ባለሃብቶቹ ሁኔታውን የሚሻሻልበትን መንገድ ለመፈለግ ቀጣይ ጥረት ቢያደርጉም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ መፍትሄ ማስገኘት ከሚያስችል ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችሉ መቅረታቸውን መግለጫው ጨምሮ አመልክቷል። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ ገዥ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።