በአዲስ አበባ የሚገኙ አስር ኤምባሲዎች፣ በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ተካሂዶ በነበረው ግጭት ተሳትፈው የነበሩ ሁሉም ወገኖች የሰላም ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና አሉ ያሏቸውም ተግዳሮቶች በንግግር መፍትሄ እንዲያገኙ ጥሪ አድርግዋል።
የአውስትራሊያ፣ ከናዳ፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድ፣ ኒው ዚላንድ፣ ኖርዌ፣ ስዊዲን፣ እና እንግሊዝ ኤምባሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተካሄደ ወዲህ በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች ሰላምን ለማምጣት ያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል።
ስምምነቱ የተፈረመበት አንደኛ ዓመት፣ የተመዘገቡ መልካም ውጤቶች የሚደነቁብት እንዲሁም ተግዳሮቶች እንዳሉ እና ሰላምን ለማረጋገጥ ጥረቶች በእጥፍ መቀጠል እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚወሠድበት መሆኑን ኤምባሲዎቹ በጋራ መግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየቀጠለ ያለው ሁከት እና በሌሎችም በርካታ አካባቢዎች የቀጠሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስደንጋጭ ናቸው ያለው መግለጫ፣ ሲቪሎች እንዲጠበቁ እና ሁሉን አቀፍ ንግግር እንዲካሄድ ጥሪ አድርጓል።