ሩሲያ፣ ዩክሬን በኩርስክ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የኒውክሌር እጣቢ ቆሻሻ ማከማቻ ቦታ ላይ፣ ጥቃት በመፈጸም ጉዳት አድርጋለች ስትል ዛሬ ከሳለች፡፡
የሩሲያ አየር መከላከያ ዛሬ ቅዳሜ አክሎ በሰጠው መግለጫ በአጠቃላይ ስምንት የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖችን) መትቶ ማውረዱን አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ምሽት በሃይል ማመንጫው ላይ ያነጣጠሩ ፈንጂዎችን የታጠቁ ሶስት የዩክሬን ድሮኖች፣ የጣቢያው አስተዳደር ህንጻ እና የኒውክሌር ቆሻሻ ማከማቻ መጋዘንን መምታት መቻላቸውን አመልክቷል፡፡
የኩርስክ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የፕሬስ አገልግሎት ትናንት ዓርብ ጥቃት መድረሱን አረጋግጦ፣ ነገር ግን የደረሰ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌለና ሥራውንም የቀጠለ መሆኑን ለጋዜጠኞች ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በምስራቅ ዩክሬን ዶኔትስክ ክልል በምትገኘው ቁልፏ የአቭዲቪካ ከተማ አቅራቢያ ከባድ ውጊያ መቀጠሉን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ሩስቴም ኡሜሮቭ ቅዳሜ ዕለት ለአሜሪካው አቻቸው ሎይድ ኦስቲን ሩሲያ በአቭዲቪካ ወደ 4,000 የሚጠጉ ወታደሮችን አጥታለች ሲሉ መናገራቸውን የኪየቭ የመከላከያ ሚኒስቴርን ጠቅሶ አሶሴትይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡