በዴስቲኒ ኢትዮጵያ አዘጋጅነት፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 50 ተጽእኖ ፈጣሪዎች ወይም የሐሳብ መሪዎች፣ ለስድስት ወራት ባካሔዱት ዝግ ስብሰባ፣ ኢትዮጵያ ወደፊት ሊገጥሟት ይችላሉ ባሏቸው ዕጣ ፈንታዎች ዙሪያ መክረው፣ “አራት ቢኾኖች” ያሏቸውን መዳረሻዎች አስቀምጠው ነበር።
ሰባራ ወንበር፣ ዐፄ በጉልበቱ፣ የፉክክር ቤት እና ንጋት የተሰኙ እና በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች መነሻ በማድረግ፣ በቀጣይ 20 ዓመታት ምን ሊከሠት እንደሚችል የሚያመላክቱት መዳረሻዎች፣ ለኢትዮጵያ የተሻለ ዕድል እንዲመጣ መወሰድ ያለባቸውን ርምጃዎች እንደሚያመላክቱም ተገልጾ ነበር።
ሰባራ ወንበር፥ ኢትዮጵያ ላሉባት ችግሮች የሚሰጠው ምላሽ፥ የተገደበ፣ ለችግሩ የማይመጥንና በቀላሉ የሚሽመደመድ የ“ቢኾን መዳረሻ” ነው፡፡ ዐፄ በጉልበቱ፥ ማን አለብኝነት፣ ዓምባገነንነት እና ፈላጭ ቆራጭነት የሚነግሥበት የ“ቢኾን መዳረሻ” ነው፡፡ የፉክክር ቤት፥ እኔ እበልጣለኹ በሚል የፉክክር መንፈስ የተሞላ እና ክልሎች የራሳቸውን ጡንቻ የሚያፈረጥሙበት የ“ቢኾን መዳረሻ” ሲኾን፣ አራተኛውና በንጋት የተመሰለው መዳረሻ ደግሞ በውይይት፣ በእርቅ እና በተቋማት ግንባታ ላይ የተመሠረተ አካሔድን የሚያሳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በወቅቱ ለነበሩባት ተግዳሮቶች አማራጭ ምላሾችን ያመለክታሉ የተባሉት እነዚኽ አራት ቢኾኖች (Scenarios) ወይም መዳረሻዎች፣ ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ ከተደረጉ በኋላ ባለው ሦስት ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ዐዲስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ተፈጥረዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሔደው ጦርነት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች ክልሎች ዐዲስ የተቀሰቀሱ እና የቀጠሉ ነባር ግጭቶች፣ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ለዓመታት የዘለቀው ድርቅ፣ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት እና ለአእላፋት ዜጎች ከቤት ንብረት መፈናቀል ምክንያት ኾነዋል።
ከዚኽ በመነሣት፣ ከተለያየ የፖለቲካ አመለካከት፣ ብሔር፣ ጾታ እና ሃይማኖት የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በስምምነት ካስቀመጧቸው ዕጣ ፈንታዎች ውስጥ፣ ኢትዮጵያ በየትኛው መንገድ ላይ እየተጓዘች ነው የሚለውን ጥያቄ፣ በምክክሩ ተሳታፊ ለነበሩት የ“ሴናሪዮ ቡድን” አባላት እና የምክክሩን ሒደት ላስተባበረውና በተቀረፁት መዳረሻዎች መሠረት ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሔድ ለሚንቀሳቀሰው “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” ጥያቄዎችን አቅርበንላቸዋል።
ከተሳታፊዎቹ አንዱ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) ፕሬዚዳንት፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ኢትዮጵያ፥ ቀስ በቀስ በሚደረግ የተቋማት ግንባታ ይደረስበታል በተባለ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ከተመሰለውና ብቸኛ በጎ አማራጭ ኾኖ ከቀረበው “ንጋት” በተቃራኒው እየሔደች ነው፤ ይላሉ።
ፕሮፌሰር መረራ፣ ኢትዮጵያ፥ ተስፋ ሰጪ ከኾነው ንጋት በተቃራኒ ወደተቀመጡት ሦስት የቢኾኖች መዳረሻዎች እየተጓዘች ስለመኾኗ የሚያመለክቱ፣ ከሰላም እና ጸጥታ፣ ወቅታዊ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ጋራ የተያያዙ ምክንያቶች እንዳሉ ጨምረው ያብራራሉ።
ደቡብ አፍሪካ፣ ረዥም ዘመን ያስቆጠረውን የፖለቲካ ቀውሷን ለመፍታት በተቸገረችበት ወቅት፣ አገሪቱ እንዳትበታተን ቁልፍ ሚና መጫወቱ ከሚገለጽለት ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የተወሰደውን የቢኾን መዳረሻ ያሰናዳው “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” አስተባባሪ ዶክተር ንጉሡ አክሊሉ ግን፣ በፕሮፌሰር መረራ ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ አይስማሙም። በርግጥ፣ ኢትዮጵያ እያሳለፈች ያለችው ውጥንቅጥ፣ በቀላሉ ወደ ንጋት የሚወስድ እንዳልኾነ አቶ ንጉሡ አልሸሸጉም፡፡ ኾኖም፣ ለንጋት የተሰጠው የጊዜ ገደብ 20 ዓመት እንደመኾኑ፣ ወደ ንጋት ለመዳረስ፣ አሁንም ተስፋ እንዳለ፣ አስተባባሪው ያመለክታሉ።
ዶክተር ንጉሡ ተስፋ የጣሉበት “የንጋት መዳረሻ” ፣ በውስጡ የያዛቸው 12 መሠረታዊ መስፈርቶች አሉ። ከእነዚኽ መካከል፣ የዜጎች በኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ላይ በቀናነት መነጋገር መቻል፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የድርድር ሒደት፣ ነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ መኖር፣ የጠንካራ ተቋማት ግንባታ፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሚደረጉ ሚዛናዊ ውይይቶች እና የኢኮኖሚ ዕድገት እንደ ማሳያ ተጠቅሰዋል።
በዚኽ ረገድ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮች የመግዘፋቸውን ያህል፣ የንጋት መንገድን የሚያመላክቱ፣ ወደ ሰላም እና መረጋጋት ሊወስዱ የሚችሉ በጎ ጅምሮች እና ተቋማዊ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም ማስተዋል ይገባል፤ ይላሉ ዶክተር ንጉሡ፡፡ የሀገሪቷን ችግሮች ከጠመንጃ አፈ ሙዝ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶች፣ “ለንጋት መንገድ ጠራጊ ናቸው፤” ሲሉም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ለምትገኝበት የፖለቲካ አጣብቂኝ መፍትሔ ለማዋጣት የተጠነሰሰው “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” ፣ ኹሉን አቀፍ በኾነ ሒደት ያሳካውን ምክክር እና በሪፖርት መልክ ይፋ ያደረጋቸውን የኢትዮጵያ አማራጭ መዳረሻዎች ያሰናዳው፣ ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ፣ የቢኾን አማራጭ መዳረሻዎችን በጥቅም ላይ አውለው የፖለቲካ ቀውሶቻቸውን መፍታት ከቻሉ እንደ ኮሎምቢያ፣ ጓቲማላ፣ ታይላንድ እና ሜክሲኮ የመሳሰሉ ሀገሮችን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ነው። ዋና ዓላማውም፣ ኢትዮጵያን እያጋጠሟት ያሉት ፈተናዎች ምንድን ናቸው? ከፈተናዎቹስ አንጻር ያሉት መፃኢ ዕድሎች ምን ምን ናቸው? ከእነዚኽ መካከል ለኢትዮጵያ የተሻለ ዕድል እንዲመጣ መወሰድ ያለባቸው ርምጃዎችስ የትኞቹ ናቸው? ለሚሉት ጥያቄዎች፣ ግልጽ እና ገንቢ መፍትሔ ለማፈላለግ እንደኾነ ተቋሙ ያብራራል።
አስተባባሪው ዶክተር ንጉሡ የጠቀሷቸውን ተቋማት ጨምሮ፣ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማትንም መገንባት አልተቻለም፤ ሲሉ የሚከራከሩት ፕሮፌሰር መረራ እንደሚገልጹት፣ “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” ያሰባሰበው ቡድን በዝርዝር ባስቀመጣቸው እያንዳንዱ የቢኾን መዳረሻ አማራጮች (Scenarios) መሠረት፣ አሁን በኢትዮጵያ ፖሊቲካ ውስጥ የሚታዩት ችግሮች እና ተግዳሮቶች፣ ኢትዮጵያ ወደ ንጋት እንዳትጓዝ ማነቆ ኾነዋል፤ ይላሉ።
ሌላው በቢኾን መዳረሻ አማራጮች ቀረፃ ወቅት ተሳተፊ የነበሩት ምሁር፣ ዶክተር አርካ አቦታ ናቸው። ዶክተር አርካ፣ በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ክፍል መምህር ሲኾኑ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎችንም ያስተምራሉ። ምሁሩ እንደሚያስረዱት፣ ኢትዮጵያ ወደ ንጋት እየተጓዘች ነው፤ ማለት የሚቻለው፣ ከግጭት ነፃ መውጣትንና በሰላማዊ መንገድ መታገልን ጨምሮ፣ በንጋት ውስጥ የተካተቱት 12ቱም ነጥቦች ሲፈጸሙ ነው፡፡ ዶክተር አርካ አያይዘውም፣ በተለይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ባለፉት ሦስት እና ከዚያም በላይ ዓመታት የሚስተዋለው ሒደት፣ “አንገቱን ያላጠናከረ ሕፃን ልጅ ዐይነት ነው፤” ይላሉ።
ዶክተር አርካ፣ ከኢኮኖሚውም አንጻር፣ በንጋት የቢኾን መዳረሻ እንደተቀመጠው፥ ምጣኔ ሀብት እያደገ፣ የግሉ ተሳትፎ ከመንግሥት ካፒታል እድገት ጋራ ተመጣጥኖ እየተጓዘ እና ሙስናን የሚያጠፋ ሥራ እየተሠራ እንዳልኾና ይልቁንም፣ በተቃራኒው እየተጓዘ እንደሚገኝ ያመለክታሉ።
ዶክተር አርካን ከሁሉም አብልጦ የሚያሳስባቸው ግን፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፥ “ከቅራኔ እና ከጥላቻ ይልቅ የይቅርታ እና እርቅ አስተሳሰቦች በማኅበረሰቡ ዘንድ፣ እንዲሁም በመደበኛ እና ማኅበራዊ መገናኛዎች በየዕለቱ ተቀባይነታቸው እየጨመረ ይመጣል፤” ከሚለው የንጋት መዳረሻ ነጥብ፣ በእጅጉ እየራቀ መሔዱ ነው።
በምክክሩ የተሳተፉትና ያነጋገርናቸው የሐሳብ መሪዎች፣ የኢትዮጵያ የቢኾኖች መዳረሻዎች ተብለው የተቀረፁት አማራጮች እንደታሰበው፣ ወደ ሕዝቡ ገና አለመዝለቃቸውና የጥናቱ ተሳታፊ የነበረው መንግሥትም እየተገበረው አለመኾኑ እንደሚቆጫቸው ይገልጻሉ። “ሰነዱ በማኅደርነቱ ብቻ ተንጠልጥሎ ቀርቷል፤” ሲሉም ይሟገታሉ።
የ“ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” አስተባባሪ ዶክተር ንጉሡ ግን፣ ተቋማቸው፥ ከሃይማኖት አባቶች፣ የታሪክ ባለሞያዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ወጣቶችን ጨምሮ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋራ አሁንም ውይይቶችን ሀገራዊ ምክክሮችን እያካሔደ እንደኾነ ገልጸዋል። በተለያዩ ጊዜያት ሊፈጠሩ ይችሉ የነበሩ ግጭቶችን መግታት የቻሉ፣ ተፃራሪ ሐሳቦችን ያስታረቁና መስማማትን የፈጠሩ ልዩ ልዩ ውጤቶችንም ማየት ችለናል፤ ይላሉ። ይህ ከኾነ ታዲያ፣ የኢትዮጵያ ችግር ለምን እየተባባሰ ሔደ? ሀገራዊ ምክክሮቹ፣ ከችግሮቹ እና ተግዳሮቶቹ ይልቅ ለምን ገዝፈው መውጣት አልቻሉም? ለሚሉት ጥያቄዎች፣ ዶክተር ንጉሡ ሲመልሱ፥ “ለዚኽ ተጠያቂው የፖለቲካ ባህላችን ነው፤” ይላሉ።
ፕሮፌሰር መረራም ተመሳሳይ ምላሽ አላቸው። ከሦስት ዓመት በፊት በ “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” ሥር ተሰብስበው፣ የኢትዮጵያን የቢኾን መዳረሻ አማራጮች የቀረፁ የሐሳብ መሪዎች፣ ዛሬ በድጋሚ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ መቀመጥ መቻላቸውንም ይጠራጠራሉ።
ይህ ከኾነ ዘንድ፣ በኢትዮጵያ ለዓመታት የተከማቸውን የፖለቲካ ችግር፣በልሂቃን መካከል ያለውን አለመግባባት እና አለመተማመን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት? ስል “የንጋት መንገድ አልተሳካም” የሚሉትን ፕሮፌሰር መረራን ጠይቄያቸዋለኹ።
ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት እና የንጋትን መንገድ ለመጀመር፣ “አሁንም ይቻላል፤” የሚሉት ዶክተር አርካም በበኩላቸው፣ መንግሥት እና ለብዙ ግጭቶች መንሥኤ እየኾነ ነው ያሉት ዐዲሱ የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ፣ እንዲሁም የተለያዩ አካላት ሓላፊነታቸውን ከተወጡ የንጋትን መንገድ መጀመር ይቻላል፤ ይላሉ።
ዶክተር ንጉሡም እንዲሁ፣ በሀገራዊ መግባባቱ አስፈላጊነት መስማማት ብቻ ሳይኾን፣ አሁን፥ እንደ “ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች እና መንግሥት በዐዋጅ ያቋቋመው የኹሉን አሳታፊ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ እየሠሩበት ያለ ጉዳይ እንደኾነ ያሰምሩበታል። በተለይ፣ እስከ አሁን ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም፤ ያሉት እርቅ እና ይቅርታ፣ በሚገባ ተቋማዊ ቅርፅ ይዘው መጀመር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በ“ዴስቲኒ ኢትዮጵያ” አስተባባሪነት፣ ከሦስት ዓመት በፊት በተዘጋጀው የኢትዮጵያ የቢኾን መዳረሻ አማራጮች ላይም፣ በብቸኝነት አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ያሻግራታል፤ ተብሎ የታመነበት ንጋት፣ ያዘለው ተስፋም ይኸው ነው። ሕጋዊ ተቋማት ማሻሻያዎችን አድርገው፣ የእርቅ ሒደቶች ተጠናክረው፣ ማኅበረሰባዊ ቅራኔዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተፈተው፣ ከቅራኔ እና ከጥላቻ ይልቅ የይቅርታና እርቅ አስተሳሰቦች ተቀባይነታቸው ጨምሮ፣ በጋራ ዕሤቶች ላይ የተመሠረተ አንድነትን መፍጠር። ይህ ዕጣ ፈንታ፣ በኢትዮጵያ ይሳካ እንደኾን፣ በጊዜ ሒደት የሚታይ ይኾናል።